Tuesday, August 31, 2010

የዳላስ ወጣቶች

እንኳን ድስ ያለን የዳላስ ወጣቶች ስብሰባ ጠርተው ሕዝብ ጋብዘው አነጋገሩ

ሳᎀኤል ሽፈራው/ከዳላስ

በአካባቢያችን አንድ አበይት ጉዳይ ተከናወኑ። ይኸውም የወጣቶች መደራጀት ሲሆን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ በመሆኑ እሰየው እንላለን። ለዚህ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ያበቃን የኩነቱን አበይትነት ከታሪክአዊ አመጣጡ ጀምሮ ስለምናውቅ ነው። ዳግም የዳላስ ወጣቶች እንኳን ደስ ያላችሁ ስንል ያለፈ የወጣቱን አኩሪና አንጸባራቂ ኢትዮጵያዊ የተጋድሎ ታሪክ ስለምናስታውስ ነው።

በኢትዮጵያ የአርበኝነት ገድል በየትውልዱ የተነሱ ወጣቶችና የኢትዮጵያ ሴቶች ለዚያች አገር መቀጠል፣ በነጻነት ኮርታ መኖር፣ ዋነኛ ተዋንያን ነበሩ። ያንን ከዘመን ዘመን የተላለፈ አኩሪ ገድል ስናስታውስ ላለፉት አመታት ያየነው የተፋዘዘ ሁናቴም ሆነ፤ አገርን የሚጠሉ ሐይሎች የአገሪቱ አራጊና ፈጣሪ ሆነው ሲገኙ ለዚያ ያበቃቸው የወጣትና የሴቶች ታሪካዊ ተሳትፎ በመጓደሉ እንደሆነ በመተከዝ እናስታውሰዋለን።

ከታሪክ

የዘመነ መሳፍንት ማብቂያ መባቻ ጀምሮ የካሳ በቋራ መነሳትና ለ20 አመታት በክልል ተከፋፍላ የቆየችን አገር መልሶ አንድ ለማድረግ በተካሄደው የአንድነት ዘመቻ በእድሜ ጎልማሳ የነበሩት ካሳና ዋና ፊታውራሪ ሆነው ያንን ተጋድሎ የተሸከሙት የጦር አበጋዝ ገብርየ፤ በአፍላ የወጣትነት እድሜ ክልል እንደነበሩ ታሪክ ይዘክረናል። ከቴወድሮስ ተከትለው ንግስናውን የወሰዱት ዮሐንስም በዋና የጦር አበጋዝነት ያገለገሏቸው አርበኛው ራስ አሉላም ቢሆን ይኸው ወጣት በሚያሰኘው የእድሜ ክልል እንደነበሩ ታሪክ ያጫውተናል።

ታሪክን ዋቢ አድርገን ይህን የምንደረድር፤ አሉ እንድንባል ወይንም ለድለላ አለያም ሽሙጥ ከጅሎን ሳይሆን የወጣቱ ተሳትፎ እስከየት የዘለቀ እንደሆነ ለማሳየት ነው። ዛሬ ይህን ደስታችንን ስንገልጽም ወጣቶች በዚህ ከቀጠሉ የማይናቅ አስተዋጸኦ ሊያበረክቱ መቻላቸውን ከወዲሁ ለመጠቆምም ነው። ታዲያ በርቱ ተበራቱ ስንል የኢትዮጵያ ወጣት ላለፉት ፳  አመታት ተፋዞ በመቆየቱ ይህ የዳላስ ወጣቶች ጅማሮ ምናልባት አንድ የታሪ ቡቅር ጠንሳሽ ሊሆን ይችላልና ነው።

እኛም በመካከለኛ እድሜ የምንገኝም ኖንነ የሽምግልናውን ቋጥኝ የጀመርነው የወጣት ልጆቻችን መሰባሰብና ለማህበራዊ ወይንም የጋራ ጉዳይ ለመከወን መነሳሳትን ትልቅ እርምጃ ወደፊት በመሆኑ፤ እንድናበረታታ ግድ ይለናል። የወጣቶች ትናንትም ሆነ ዛሬ ለጋራ እንቁም ማለት ወጤታማነቱን ያለፉ ታሪካችን ስላስተማሩን። በድህነት የመጨረሻ ጫፍ ላይ ያለች አገርንና፣ በጭቆና ቀንበር ተቀፍድዶ የተደየነን ሕዝብ የነጻነት ተስፋው መጭውና አዳጊው ትውልድ ነውና በርቱ ተበራቱ በሉልን።

በ1928-33 ብተካሄደው ጠላትን ከአገር የማስወጣት ተጋድሎ አንድ አቢይ ነገር ተፈጸመ። ጊዜው 1930 በበልግ ወራት ነበር። ልጅ በላይ ዘለቀ በጊዜው የ24 አመት ወጣት ሲሆን፣ ምክትል ታናሹ እጅጉ ዘለቀ 22 አመት እንደነበር ይነገራል። ከበታች የሁለቱም ታናሽ በናት የሚገናኛቸው ሽፈራው ገርባው የ19 አመት ወጣት ነበር። እነዚህ ሦስት ወጣት ወንድማማቾች ደብረማርቆስ የነበረውን የጠላት ጦር ይከባሉ። ወጣቱ የጋሜወች መሪ የነበረው ሽፈራው የሱን መሰል ወጣት ጦር ይዞ ስለነበር። ሁለቱ ታናናሽ ወንድሞቹን ይዞ ትልቅ ሐይል ይያዘውን የጠላት ጦር የገጠመው ልጅ በላይ ዘለቀ በእኩለ ቀን ድል መቶ የጠላትን ጦር አሸብሮና የሚችለውን መሳሪያ እስከ ባንዳው ማርኮ ብቸና ገባ። ዜናው በአውሮፓ ጋዜጦች በሰፊው መወራቱ ያሳፈረው ጥሊያን። ደካማ እናታቸውንና የበላይን ሚስት ከመኖሪያ ቤታቸው በባንዳ አስከብቦ ይዞ ወደሮማ ላካቸው። እኒህ ሁለት እናትና ባለቤቱ በኋላ ሊመለሱ ችለዋል።

በምእራብ ሸዋ በቀለ ወያና፣ በገረሱ ዱኪ መሪነት ጠላት በአምስት አመት ዘመን እፎይታ ሳያገኝ እንገብግበው እንዳባረሩት ሌላ ታሪክ አስተምሮናል። እነዚህ ሁለት ወጣት አርበኞች ከጦርነቱ በፊት በመሪነት ሊታወቁ ቀርቶ፤ መኖራቸውን ከፈጣሪና ከቤተሰብ ውጭ የሚያውቅ አልነበረም።

ስለወጣቱ ስናወሳ ምንግዜም በአይነቱና ለሕዝብ ብሎ በመነሳት ብሎም መስዋ’እትነት በመክፈል ለታሪክ አሻራውን የለገሰው የየካቲት አቢዮታዊ የኢትዮጵያን ወጣት ሳናወሳ ግን ልናልፍ ይቸግረናል። ዛሬ ወጣቶ በዳላስ ስብሰባ ጠሩን ስንሰማ የነ ቲቶ ሕሩይን፣ የነሱራፌል የካባን፤ የነ ሳᎀኤል ሽፈራውን። ብሎም ከፍ ከፍ ያሉትን ወጣት ምሁራን ገድል፤ የነ ተስፋየ ደበሳይን፤ ግርማቸው ለማ፤ ዮሐንስ ብርሐኔ እና አያሌ ሰማእታት ወጣቶችን ገድል ዘከረን። ይህ የዛሬ የዳላስ ወጣቶች እራስን ማደራጀት በእጅጉ አስደስቶናል። አይዟችሁ፣ በርቱ ተመንደጉም እንላለን። ልናሳስባቸውም የምንፈልገው ቁጥረ ብዙ የሆኑ እዚህ ተወልደው ያደጉ ብዙ ወጣት ምሁራን እየወጡልን ስለሆነ፤ ይህን ተስፋ በማየት መጭው ዘመን የተነቃቃ እንደሚሆን አልተጠራጠርንም። ወጣቶችም አቻ ወንድሞቻቸውን ከጎናቸው ያሰልፉ ዘንድ እኛ ከወጣት እድሜ ክልል ያለፍን ሁሉ ልንተባበር ይገባል እንላለን።

ዛሬ የዳላስ ወጣቶች እንዳለፉት ጀግኖች በር ከፋች ናቸው። በር ከፋች ስንል አዲስ ብስራትን የመደራጀት ዜናን ስላሳዩን ለማለት ነው። ለአመታት የወጣቱ ተሳትፎ የቀዘቀዘውን ያክል፤ይህ አንድ ምእራፍ ከፋች እንደሚሆን አንጠራጠርም። በድጋሜ በርቱ ተበራቱ በማለት በሚቀጥለው ዜና እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን



No comments:

Post a Comment