Wednesday, March 16, 2011

Judgement comes from experience, and experience comes from bad judgement. (Simon Bolivar)

ዘመነ አብዮት

በአገራችን ሕዝባዊ አብዮት ተነስቶ አንድ ስርአትን ቀይሮ የተነሳበትን አላማ ግብ ሳያደረስ በሁለት ተከታታይ ቀማኞች ተጠልፏል። ለአለፉት ሦስት ወራት እየተናጠ ያለው የሰሜን አፍሪካ ሕዝባዊ አብዮት ግን የት ሊቆም እንደሚችል ገማች የለም። መቸም አንባገነኖች የመጨረሻዋ ሰአት ደርሳም ይበቃልን አያውቁምና ሞሐመድ ጋዳፊ አሁንም የስልጣን ዘመኔ ይቀጥላል በሚል የእንቢተኝነት አመጽ ተሰማርቶ ሕዝብን እየፈጀ ነው። የጋዳፊ ጭፍጨፋን ድፍን አለም በመቃወም ላይ መሆኑንና አይቀሬ ውድቀቱ ጥይት በተኮሰ ቁጥር መቃረቡን ከሱ በቀር ለአለም ገሐድ እየሆነ መጧል። አሁን አሁን እየገረመኝ የመጣው የሌሎቻችሁን አላውቅም እነዚህ አንባ ገነን የሚባሉና የሆኑ ሁሉ ከአንድ እናት የተፈጠሩ ይመስል ባሕርያቸው ተመሳሳይ ሆነብኝ።፡ተቃውሞ ሲነሳ ለኔ ይደርሳል የሚለውን ፈጽሞ አይታሰባቸውም። ደግሞም ያች ቀን ደርሳ የመውጫ በራቸው ተበርግዶም ሰው መግደልን፤ ንጹሐንን መጨረስን ይሁነኝ ብለው ያረጉታል። አጉስጦስ ፔኖቸ ሞት ከደጃፉ ቆሞ እየጠበቀው አንድም ሰው አልገደልሁም በማለት እስከ ፍርድ ቤት ደረሰ። ከሰማኒያ አመት በላይ የሆነው ፋሽስት ፔኖቸ ለንስሐ የሚያበቃ አጋጣሚና ግዜን አግኝቶ ሳይጠቀምባት፤ ከደጃፉ ቆሞ ይጠብቅ የነበረው ሞት one way ticket አስይዞ ወሰደው። መንግስቱ ሐይለማሪያም የስደት ኑሮ እየኖረም፤ አገርና ሕዝብ እንደጎዳም ልቦናው እያወቀ አሁንም ትንኝ እንኳን አልገደልሁም እንዳለ የንስሐ ግዜውን ባልባሌ እያሳለፋት ነው።

ነገርን ነገር ስላነሳው እነኝህን የታሪክ አተላወች ጠቀስሁ እንጅ፤ ለነገሩ ያልተቋጨው ያገራችን የየካቲት አብዮት ዳግም ሊዳስሠን እየከጀለ ለመሆኑ በሰሞኑ የአርባ ምንጭ የሕዝብ መንቀሳቀስና በአዋሳም ያለለው ግር ግር ሌላ ምልክት መሆኑ አይቀሬ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረኛና ጠባብ ብሔርተኛ አናሳ ቡድን ላይገዛ በምርጫ 97 እንዳሳየ ሁሉ፤ ዛሬ በከባቢ ጎረቤቶቹ የተካሄደውና እየተካሔደ ያለው የአልገዛም ባይነትና ጀግንነት ልቡን እያሸፈተው ለመሆኑ ጥርጥር የለም። የሚጠራጠሩ ቢኖሩ የዚህ ዘረኛ መንግስት ሹንባሾችና እናገኛለን ብለው በመንደፍደፍ ላይ ያሉት አዲሶቹ ተስፈኞች ብቻ ናቸው። አሁንም ነገርን ነገር ያነሳዋልና አንድ ከዳላስ የሄዱ አገር ጎብኝ በሌላ እስክንመለስበት ስማቸውን ማንሳቱን ስላልፈለግን አንባገነኑን ስርአት በማወደስ “ከዚህ የተሻለ የለም። መቸም ከሰማይ መና አይወርድልንም” በሚል አባባል ከጎናችው የተቀመጡ ቢጤወቻቸውን ሳይቀር ያስደነገጠ በመሆኑ የስላቅ ሳቅ ሲስቁ አስተውለናል።
አንባገነኖች ተሰቅስቀው እስኪነሱ አያምኑምና የኛውም ትንሹ መለስ በሰሞኑ ከአንድ ሴት ወጣት ጋዜጠኛ ለቀረበለት ቃለምልልስ የሰነዘረውን ሳይ ከልክ በላይ አስደመመኝ። ልቡ ከላይ ታሽ እየፈረጠ ስልጣንን ግን ለማቆየት ያውም ሕዝብ የጠላው ሰው፤ ሕዝቡ መርጦናል ሢል ማየቴ ሁሉም አንባገነኖች ከፔኖቸ እስከ ሙባረክና መለስ፣ ለታሪካቸው ለቤተሰቦቻቸው፣ ለራሳቸው ምንም የማያስቡ እንደአህያዋ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አይነት ናቸው።

ዛሬ በሁሉም አቅጣጫ መነሳሳት በመጀመሩ፣ እዚህ ዳላስ ሁለት እንግዶች ተጋብዘዋል። አቶ ረዳ መሐሪና ዶክተር ታዬ የኢሕአፓ ዴሞክራሲያዊ አመራር አባላት ሲሆኑ። አገርቤት ስላለው ሁናቴና የተቃዋሚወች ትብብር እንዲሁም የዳግም አብዮት አይቀሬነትን አስመልክቶ ሊያወያዩን እሁድ ማርች 20, 2011 ይመጣሉ።

አቶ ረዳ ማህሪ ወይንም በሜዳ ስማቸው ፀሐዬ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ሰራዊትን (ኢሕአሰ) ከመሰረቱት ከትቂቶቹ ቀደምት ታጋዮች አንዱ ሲሆኑ 1966 ዓ.ም ከዋሽንግተን ከተነሱት የዚያን ግዜ ታጋዮች ከነ ክፍሉ ተፈራ፣ ለገሰ አጃቢ፣ አይንሸት ተፈሪ (የጀኔራል ተፈሪ ባንቲ ልጅ)፣ ሙሉጌታ ሱልጣን፣ ሙሉጌታ ዜና ጋር በመሆን ብዙወቹ ወደከተማ ሲገቡ ፀሐየና ብርሐነ መስቀል እረዳ ከሌሎች ታጋዮች ጋር በመሆን ወደ አሲንባ ተጉዘዋል። ከዚያን ያፍላ የወጣት ጊዜ ጀምረው አሁንም በትግሉ ጎራ ያሉ ታጋይ በመሆናቸው፤ ትውልድ ሊያውቅ የሚችለውንም ለማሳወቅም ሆነ ዳግም አብዮትን ለማምጣት ለሚደረገው እርብርቦሽ አይነታ የታሪክም ሆነ የልምድ ባለጸጋ አርበኛ ታጋይ ናቸው።

ዶክተር ታዬ ዘገየ ኢሕአፓ ወልዶ ካሳደጋቸው ታጋዮች አንዱ በመሆናቸው ብሎም በአመራር ብቃትና ታጋይነት ከልጅነት እስከዛሬ በትግሉ ጎራ በመገኘት የመሩ የታገሉና ያታገሉ ሰው ናቸው። አሁንም ስለመጭ ሕዝባዊ አብዮትም ሆነ የሕዝብ መነሳሳትን ለመፍጠር ለሚደረገው የዴሞክራሲ ትግል ለመወያየት ስለሚመጡ በዚህ በዳላስ የምትኖሩ ወገኖች ሁሉ ተጋብዛችኋል።

ይህን ጊዜ መጠቀም አስፈላጊ ነው። የየካቲት አብዮት ግቡን መቶ ዳግም ጭቆና የሌለባት አገር መመስረት አስፈላጊ ነው። መጭ ትውልዶች ለመብት በሚደረግ ትንንቅ መሞት መንገላታት አይኖርባቸውም።

ይህ ጥሪና ውይይት እንዳያመልጣችሁ ጥሪ ይድረስ ይላሉ አዘጋጆች።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ያቸንፋል!!!


No comments:

Post a Comment