Tuesday, November 23, 2010

Joe Paterno,,, Act like you expect to get into the end zone.

የከሸፈው የወያኔ/ኢሕአዴአግ ስብሰባ በዳላስ

ይህን ስብሰባ አስመልክቶ በቅንጫቢ የወጣ ምስል ቀደም ብሎ ልከን ነበር። የተሟላ ባለመሆኑ በተለየም ያነን ምስል እንዲታይ የፈለግነበት ዋና ምክንያት የገዥው አንባገነን መንግስት ደጋፊወች ምን ያህል በትእቢትና በብልግና እንደተካኑ ለማሳየት ነበር። በዚህ መጣጥፋችን ደግሞ በመላ አለም ነዋሪ ለሆነው ወገናችን አንድ ተምሳሌ ሆኖ ያገለግላል ብለን ስላመን የቀኑን ዘገባ በአቅማችን እናቀርባለን። አንዳንድ ባካባቢም ሆነ በውጭ የነቀፉን ግለሰቦች መብትና ነቀፋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በኛ እምነት ይህን አንባገነን መንግስት በደረሰበት ሁሉ መታገል አስፈላጊም ተገቢም ነው ብለን በማመን፣ ያሰብነውን አሟልተናል።

በተደጋጋሚ በድሕረ ገጾች እንደገለጥነው ይህ በኢትዮጵያ ኮሚውኒቲና የተለያዩ ተቋማትን ሲቻል ሰርጎ ገብቶ መጠቅለል ሳይሆን ሲቀር በግድ ከሶና አዋክቦ መውሰድ በኛ አካባቢ የቀን ተቀን ስራቸው ሆኖ አግኝተነዋል። በተጨማሪ ሕብረተሰባችንን እርስ በእርስ ለማባላት የሌለ ልዩነትን መፍጠር፣ አሉባልታ መንዛትና እንዳይተማመን ማድረግ በሰፊው የተያዘ ስራቸው ሆኗል። ይህ ተግባር በሊሎችም አልተሞከረም ለማለት ግን አንችልም። ሆኖም ወገን በያለበት ነቅቶ መጠበቅ ያለብን መሆኑን እኛ ካየነውና እያለፍንበት ካለው ችግር እንዲማር እናሳስባለን። በፖለቲካው እረድፍ ደግሞ ሰሞኑን በኮሚውኒቲአችን ራዲዮ ጭምር ነዋሪውን በመጋበዝ ለመጭው አምስት አመት በሚደረግ ያገር ውስጥ ኤኮኖሚ ተሳተፉ የሚል ልፈፋ ለሁለት ሳምንታት ያለማቋረጥ አድርገው፣ በየምግብ ቤቱና ወገን የደርስበታል በሚባሉ ሁሉ ቦታወች ወረቀትና ማስታወቂያ ለጥፈው፤ ኢትዮጵያዊው ዜጋ ጀሮ በመንፈግ ባለፈው ቅዳሜ ኖቬምበር 13 ቀን 2010 እ.ኤ.አ በተደረገ ስብሰባ ከአባላቶቻቸውና ያባት ቤት ሲወረር በሚል ይትብሐል የቀረቧቸው ደጋፊወች በቀር ንጹህ ዜጋ ሳይገኝ ቀርቷል። ከሁሉም በላይ አገር ወዳዱ ካየነው የተሻለ ቁጥር ይኖራቸው ይሆናል በማለት የገመትነው ቀርቶ አሁንም ያው አንድ ፍሬ የምናውቃቸው ግለሰቦች ሆነው ስናገኝ፤ ምን ያህል ይህ ቡድን ሐብትና ንብረት ቢያፈስ ወገን ቂሙን ላይረሳለት መወሰኑን ካየነው ተምረናል። 

ትግሉን በሄደበት ሁሉ ደርሶ ለማጋለጥ በተያዘው አላማ፤ ይሆንልኛል ብሎ የሞከረው ያለፈው ቅዳሜ ስብሰባ ተብየው የጠባቡ ቡድን የድለላ ዘመቻ መሆኑን ለማጋለጥ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከፖለቲካ ድርጅት ደጋፍኢወች ጋር በመሆን ስብሰባው አዳራሽ ገብተው ከእውነት የራቀውን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ፊት ለፊት አጋልጠውታል።

የስብሰባው አካሄድ ከዚህ በታች ባለው መልክ እንገልጸዋለን።

ስብሰባው በሰአቱ እንዲጀመር በሊቀመንበርነት በተሰየመው ግለሰብ ቤቱን ይጠይቃል። ከአዳራሹ በተሰብሳቢነት ከመጡት የአገዛዙ ደጋፊወች አንዱ ተነስቶ ስብሰባው እንዲጀመር ለሊቀመንበሩ መስማማቱን ገለጸ።

ከወገን በኩል በታሰበው የስብሰባ ስነስራት መሰረት፤ ስብሰባው የሚጀመር ከሆነ መጀመር ያለበት በጸሎት መሆኑን ከተቃዋሚው አንድ ግለሰብ ገልጾ፤ መላ ተሰብሳቢው ይህን የሰማእታት ቀን ምክንያት በማድረግና በምርጫ 1997 ብሎም ወያኔ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ለተጨፈጨፉና ዳብዛቸው ለጠፋ ወገኖቻችን የሁለት ደቂቃ ጸሎት እንዲደረግ ተሰብሳቢውን በትህትና እንዲነሳ ጠይቆ ጸሎቱ ያለምንም ችግር ተደረገ።

ግራ የተጋቡት የአገዛዙ ደጋፊወችም ሆነ ለስብሰባው በእንግድነት የመጣው አንባሳደር ግር ስላለው ሊሆን ይችላል አብሮ መቆሙን ታዝበናል። በእርግጥ አራት ወይም አምስት የሚደርሱ ከመቀመጫቸው ያልተነሱም እንደነበሩም ታዝበናል።

ወደስብሰባው መሄዳችን ቀርቶ ከአስር እስከ አስራአምስት ደቂቃወች ሰማእታት ሲባል የሚለውን። በዜጎች ላይ የተፈጸመ ወንጀልንና የሞቱት ዜጎችም በሰላም ወጥተው ማንንም ሳይጎዱ ላቀረቡት ጥያቄ የአጋዚ ሰራዊት የመለሰላቸውን የጥይት ምላሽ አስመልክቶ ለሙታን የተደረገ የክብር ማስታወሻ መሆኑን ለማስረዳት ተሞከረ። አንባሳደሩም ሆነ ከተሰብሳቢው ያስተባበለ ሳይኖር ጉዳዩን በስድብ ብቻ ለማለፍ ከጅለው ነበር። አስከትሎም በተለየም በትግሉ ጎራ ላመታት ታግለው በዚህ ጠባብ ቡድን ታፍነው የት እንደደረሱ ያልታወቁት ታጋዮች መዳረሻን ተጠይቆ፤ መልስ ባለመኖሩ ትግሉ ቀጣይ አፈናውና ግድያውም ወያኔ እስካለ እንዲሁ የሚኖር መሆኑን ከተሰብሳቢው አንድ ወንድም አሳስቦ፤ ይህን ዘረኛና አንባገነን መንግስት መደገፍ መጨረሻው ላገርም ሆነ ለወገን መጥፎ እንደሆነና ደጋፊወች ሳይመሽ ጥግ መያዙ፣ ወይም ከወገን ጎራ መሰለፍና ለአመታት የቀረበውን የህዝብ ጥያቄ እውን ለማድረግ መታገል እንደሚገባ ተነግሯል። ሆኖም መስማት የማይፈልጉት ነገር በመሆኑ ከመቀመጫ በመነሳት ስድብና ብልግና የተቀላቀለበት ሲያወርዱ የተቃዋሚው ወገን ሕግና ስርአትን ሳያፈርስ ተከላክሎ መልእክቱን በበቂ ለማስተላለፍ ችሏል።

ከዚያ በኋላ በነበረው ጊዜ ለአርባ አምስት ደቂቃወች ያክል በመተራመስ ሰአት ሲሄድ፤ ለትርምሱ የአገዛዙ ደጋፊወች በተከራየነው አዳራሽ ለምን ዝም አትሉም በሚል ባነሱት ግርግር ነበር። በአዳራሹ ከገዥው ቡድን ደጋፊወች በላይ አገር ወዳድ ወገኖች ይበዙ ስለነበር ሳይወዱ በግድ አፈግፍገዋል።

አንድ ወጣት በዚህ መንግስት ተቀጥሮ በየመን ኤምባሲ የሰራ ከወያኔው ተወካይ እንግዳ ጋር የሚተዋወቁ መሆኑን ከነገረው በኋላ፤ ለማስገደል ሞክራችሁኝ እንደነበር አውቃለሁ፤ ነፍሴንም አትርፌ ወደስደት መጥቻለሁ በማለት ሲነግረው መልስ ስላልነበረው፤ እኔ 1972 ዓ.ም በኋላ ጠበንጃ ይዠ አላውቅም የሚል መልስ ስለሰጠው። መች አንተ ልትገድለኝ ነበር አልሁ። አንተና የበ.አ.ዴ ን ጓደኖችህ ልታስገድሉኝ ነበር ነው በማለት ሲገልጽለት። ደግሞ ደጋግሞ ተመሳሳይ ነገር በመናገር ጥያቄውን ሳይመልስለት ቀርቷል።

እንግዳው አስቸጋሪውን የዳልሳ ሁኔታ ለመግለጽ በድጋሚ በካሊፎርኒያ፣ በዲሲና በሲያትል የነበሩ ስብሰባወችን በማድነቅ፤ ዳላሶችን በማኮሰስ ለማስቆም የሞከረውም ሳይሳካ ቀርቷል። በማስከተልም እዚህ ዳላስ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ በወጉ እንኳን ቁጭ ተብሎ ለመነጋገር አለመቻሉ ያሳዝነኛል ብሏል።

በብዙ መማጸን ለእሩብ ሰአት ያክል እድል ያገኘው የእለቱ እንግዳ አገሪቱ በታሪኳ እንደዚህ ያለ አገዛዝ አልነበራትም ሲልም ተደምጧል። ይህ አበባሉ ያስገረማቸው ወገኖች በሳቅ እቤቱን ሲያሞቁት የአንባገነኑ ቡድን ደጋፊወች ጭብጨባውን አቅልጠውታል። ብዙ እድል ተሰጥቶት ሊናገር የሚገባውን ትቶ የደረቀ የዘረኞችን ፖለቲካ ለማስተጋባት ሲቀጥል በስነስራት ተገቶ ተቃዋሚው ያለውን ለማስረዳት ወደመድረክ በመውጣቱ ዳግም ያገዛዙ አቀንቃኝ ወገኖች አልጨረሰም ጥያቄ ከሆነ ማቅረብ ትችላላችሁ ያውም በሦስት ደቂቃወች ግድብ በማለት ቢማጸኑም፤ ከተቃዋሚው በኩል የተነሳው ወንድም ወያኔ ወደስልጣን ሲመጣ አገሪቱ በዘር ላይ ተዋቅሮ የተደራጀ ስርአት ሳይሆን አንድነቷን ጠብቃ የቆየች ከመሆኗም አልፎ ሰፊ የባህር በር የነበራት እንደነበረች ጠቅሷል። ይህ የታሪክ ጉድ ስልጣን ከያዘ በኋላ፤ ጎረቤትን ከጎረቤት ከማለያየት ጀምሮ በቤተሰብ እንኳን ደምና አጥንት መቁጠር ተጀምሮ እንደነበር የሚታወስ መሆኑን አስገንዝቧል። ይህን አስመልክቶ የተቸው ተናጋሪ በመቀጠል ዛሬ በአገራችን የተንሰራፋው ስርአት በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሲሆን። ማነጻጸር ካስፈለገ ሊስማማ የሚችለው በ1928 ዓ ም አገራችንን የወረረው የውጭ ጠላት ጋር ብቻ ነው በማለት ለማስገንዘብ ችሏል።

እውነትን መናገር የማያውቁትና እውነት ሲነገር የሚያንቀጥእቅጥአቸው የጠባቡ ቡድን ደጋፊወች፤ ይህን ሐቅ መቀበል ስላቃታቸው እራሳቸው የተከራዩትን የስብሰባ አዳርሽ በጩኸት አደባልቀውታል። እውነት እንዳይነገር የሚፈልጉት ወዶ ገብ ወገኖች (ቁጩ አማሮች) ከዶክተር ወንድሙ የተወሰደ ቃል፤ በዘር ሐረጋቸው ከሚዛመዱት የወያኔ ነባር አባላት በላይ ጉሮⶂቸው እስኪደርቅ ሲያቅራሩ አምሽተዋል። ሆኖም አገር ወዳዱ ዜጋ ወይ ፍንክች በማለቱ ሊያስተጋቡት የፈለጉት እንጨት እንጨት የሚል ፕሮፓጋንዳቸው ከማንም ጆሮ ሳይደርስ፤ በተከራዩት አዳራሽ አገር ወዳድ ወገኖች ያለከልካይ ለጠባቡ ቡድን ደጋፊወችና አባላት ልካችውን አሳይተዋቸዋል።

በእንግድነት ተጋብዞ የመጣው ዲፕሎማት በስም በተግባር ግን አንድም ለሾመው የዘረኛ መንግስት የካድሬ ስራ ላይ መሰማራቱ የሙያተኛ ዲፕልሎማቶችን ታሪክ የሚያጎድፍ ሲሆን። በመሰረቱ እንደ አንድ የዲፕሎማት ባሕርይ ሳይሆን አለፍ አለፍ ብሎ የሚንቦገቦግ ንዴቱን አሳይቷል። በአንድ ንግግሩ ተሰብሳቢውን share up colloquial language ይሉታል የመንገድ ቋንቋ ማለት ነው። ለማለት የፈለገው shot up ነው ይህም ቢሆን ለአንድ ዲፕሎማት የሚመጥን አነጋገር አልነበረም። ሲልም አዳምጠናል። እንደአንድ ዲፕሎማት ትእግስት ይዞ ለአገር የሚሰራ ሳይሆን እንደአንድ ካድሬ የተሰጠውን የፖለቲካ ሸቀጥ ተሸክሞ በተባለው ቦታ አራግፎ ለመመለስ በመሆኑ። ያሰበውን የሚገዛ ቀርቶ ጊዜ ሰጦ የሚያዳምጥ በማጣቱ እውነተኛ የካድሬ ባሕርያቱን አሳይቶናል።

ባንድ ወቅት መለስ ስለተቃዋሚወች ተጠይቆ ሲመልስ “እዚህ የደረስነ ዳገት ቁልቁለቱን ወርደን ነው። እነሱም እኛ በተጓዝንበት መንገድ ይሂዱና፤ ስልጣኑን ይውሰዱ” ብሎ እንደነበር ሁሉ። አንባሳደር ታየ ዳላስ ላይ ቅዳሜ ኖቬምበር13 ቀን 2010 እ.ኤ.አ  የመጨረሻ ትእግስቱን ሲያሟጥጥ “ በዋሽንግተንም ስብሰባ ጠርተን አይተናል፣ በሲያትልም እንዲሁ ጠርተን ተወያይተናል፣ በሎሳንጀለስም ደጋግመን ከኢትዮጵያውያን ጋር ተነጋግረናል፣ ዳላስ ከአንድም ሦስት ጊዜ መጠን የተሻለ ባለማየቴ አዝናለሁ። ሌሎች ከተሞች ወደ አመራር ሊመጡ የሚችሉ አግኝተናል። እዚህ ያነን ባለማየቴ አዝናለሁ” ካለ በኋላ ተቃዋሚው እንዲህ ከሆነ ያው ኢሓዴግ በሄደበት ጎዳና መሔድ እና ስልጣኑን መውሰድ እንጅ ሌላ አማራጭ ሊኖረው አይችልም” ብሎ አረፈው። ይህ ጠባብ ቡድን ዴሞክራሲ ብሎ ያላገጠ ለመጀመሪያ ትቂት አመታት እንጅ እምነቱና ተግባሩ የአንድን ቡድን የበላይነት የማስቀጠል መሆኑን ከኛ አልፎ አለማቀፍ ደጋፊወቹም የሚያውቁት ነው። ወያኔ/ኢሕአዴግ ስልጣን በሰላም ላለመስጠት ምሎ የተገዘተ ለመሆኑ ለ20 አመታት በስልጣን በቆየበት ዘመን ያሳየው ሲሆን ምርጫ ብሎ ባቧለተበት ሰኔ 2002 ዓ.ም እንዳየነው በ 99.6% ተመረጥሁ በማለት አይኑን በጨው አጥቦ ያለምንም እፍረት ለአለም ሕዝብ አውጇል። መለስና ተከታዮች እዚህ ዳላስ እንደመጣው ሁሉ፤ በኛ መንገድ ሔዳችሁ ካልሆነ በሰላም አይናችን እያየ አንለቅም የሚለውን ቃል ካዲስ አበባ እስከ ዳላስ አሰሙን ማለት ነው።

ሌላው በመጨረሻ የራሱ የወያኔ አባላት መድረኩ በተቃዋሚው ሙሉ በሙሉ መደፈር ያበሳጫቸው ስብሰባውን ትተው ከወጡና ትቂት ፍሬ መቅረታቸውን ያየ ተቃዋሚም ከወጣና የመዝጊያ ጊዜው ሲቃረብ የሰጠው አስተያየት ቢኖር የተጀመረው የልማት ጎዳና ትክክል መሆኑንና ከአፍሪካ ከዩጋንዳ ጋር የተሻለ ውጤት የታየባት ኢትዮጵያ ብቻ ናት፣ ብዙ ሕንጻወች በየዋና ከተሞች ተሰርተዋል፣ መንገድ ተቀይሷል ይህ የወያኔ ውጤት ነው አለ።

የዚህን ምጸታዊ አነጋገር ሊቀበል ያልፈለገ ወንድማችን ከአዳራሹ መውጣቱን አቋርጦ። ከአለማቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች የሚገኘው ገንዘብ ወደወያኔ ካድሬወችና አለቆች ኪስ ስለሚገባ ከውጭ ባንክ አካውንት ቀንሰው በሕንጻ ስራ ላይ ማዋላቸው አገሪቱ አደገች አያሰኝም። የአንድ አገር እድገት የሚወሰነው በዜጎች የኑሮ መሻሻል ሲደረግና ምርታማነት አድጎ ከፍጆታ ወጦ ለአገር ውስጥና አለማቀፍ ገበያ ሲውል ነው። ከአርባ አመታት በፊት መሬት በባላባቶች በመያዙ ነው ሕዝባዊ አብዮት የመጣው። ዛሬ በአገሪቱ ከአንባገነኑ ትቂት አባላት በቀር መላ ዜጎች የመንግስት ጢሰኛ እንዲሆኑ ተደርገዋል። የአገሪቱ እድገት ወሳኝ የሆነው ግብርና አሁንም ከእጅ ወዳፍ በሚሆን የምርት ተግባር እንደተሰማራ ሲሆን የሰፋፊ እርሻወሽ እድገት  ከ1960ወቹ የተሻለ ላይ አይደለም። የዚህ መሰረተ ኢኮኖም አለመሻሻል አሁንም እርሐብ በቋሚነት በያመቱ ስድስት ሚሊዮኖች ሕዝባችንን ይጎበኛል። ድጋሚ ለማሳሰብ የካድሬነት ተ ልእኮ ማሟላት  አንድ ነገር ሆኖ ሳለ የሌለ እድገትን አደርግን ማለትን ለምናውቅ አይነገረንም በማለት ትቂት ለተቀመጡና ለአንባ ገነኑ ደጋፊወች አስረድቷል። ሕንጻማ በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካም ሆነ በቅኝ ተገዥዋ ሮዴሽያ ሞልቶ ተርፎ ነበር። ኢትዮጵያውያን ለአለፉት አራት አስርት አመታት የታገሉለትን ዴሞክራሲን፣ ይፈልጋሉ፣ የአገራቸውን ነጻነትና፣ የሕዝቧን እኩልነት ይመኛሉ ያን ሕልምና አላሚወችን የገደለ መንግስት የጊዜ ጉዳይ ነው በማለት አስተያየቱን ሰጦ ወጥቷል። ከዚህ በኋላ ስብሰባ እንዳልነበረና የወያኔ ካድሬ ትቂት አጃቢወቹን ይዞ ወደተለመደው የአዲስ አበባ ምግብ ቤት ተሰይመው እንዳመሹ ዜናው ደርሶናል።

No comments:

Post a Comment