Monday, January 10, 2011

Any mind that is capable of real sorrow is capable of good. Harriet Beecher Stowe

እሕአፓን ለቀቅ

ከሳᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

“I wish they all die”  ይህን ያለው አንድ ኢሕአፓን እጠላለሁ የሚል ግለሰብ በነበረ ጭውውት መሐል አስገብቶ ነበር። አሱንም አጀብ ብለነው ነበር። ትናንት ደርጉ የቻለውን አደረገ፣ ገደለ፣ አረደ አንድ ትውልድን መተረ። ወያኔም የቻለችውን አደረገች። ጊዜ የሰጣቸው ሁሉ የመጀመሪያ ተግባራቸው ምኞታቸውን እውን ማድረግ ነው። እስካሁን እንዳየነው ትንሽ ነጥብ አመል ያለበት ሁሉ ምኞቱ በኢሕአፓ መዝመት ነው። ወያኔ ወደስልጣን ስትመጣ በአገው ግምጃቤት በስብሰባ ላይ እንዳሉ የያዘቻቸውን የኢሕአፓ አመራሮች ዳብዛቸውን አጥፍታ እስከ ዛሬም ያሉበትን ላለመናገር እንደወሰነች ነው። እውቁ ታጋይ ጸገዬ ገ/መድሕን (አበበ ደብተራው) ከጓዶቹ ጋር በወያኔና በሻብያ ጦር ታፍኖ መዳረሻው ካልታወቀ በመጭው የግንቦት መባቻ 20 አመታቸውን ይደፍናሉ። ስለዚህ የታጋይ ትውልድ መሪ ድርጅት ዝክር ልናወራ ብቃቱንም ጊዜውንም አልሰጠንምና እንዲሁ በጨረፍታ ያየን ያሸትነው ስላለ ለጊዜው የሚያውቅ የለም ብለን ሳይህን ለግንዛቤ አስበን ይህን እንድንል አሰብን።

በመጋቢት 14 1969 ተሰፋየ ደበሳይ፣ ከፎቅ ወርዶ እራሱን ሲያጠፋ በራሱ ለመጨከን አስቦ ሳይሆን ትውልድን ጀግንነትን ለማስተማር ነበር። አ’ጼ ቴወድሮስ እራሳቸውን የገደሉ እኮ ኢትዮጵያዊ አይበገሬነትን ለትውልድ ለማሳየት ለጠላት እጅ መስጠት የማትሞከርነቷን ለማስተማር ነበር። ሁለቱም ኩነቶች የኢትዮጵያዊነት የጀግንነት፣ የአይበገሬነት ተምሳሌና ኩራት ናቸው። ኢእሕአፓ ስንልም የዚያን ጀግና ትውልድ ገድል መዘከር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። አወ በየፌርማታው የለቀቁ ብዙ ናቸው። አንዳንዶችም ከጠላት ገብተው አገር አጥፊ ሆነዋል። ትቂቶቹ ዛሬም ኢሕአፓን አያሳየን እንዳሉ እናያለን።፡ከነዚህ ከፊሎቹ የሕወሐት ደጋፊወች መሆናቸውን ካሳወቁና በጠላት የፓስፖርት ቁጥር እንደሚታወቁ እርግጥ ነው። ታዲያ እነኝህን ደባልቆ ቃልኪዳናቸውን ሳያፈርሱ፣ ማተባቸውን ሳይበጥሱ ከቀጠሉት መቀላቀል ከባድ ስሕተት እንለዋለን።

መቸም በኢትዮጵያ ይህን መከረኛ ድርጅት ሳይኮንን መድረክ የሚረግጥ ባይኖርም። ኢሕአፓ ግን የሰማእታት ገድል የታየበት ለጨቋኞች የእንቢተኝነት ፊታውራሪና አስተማሪ ድርጅት እንጅ አጥፊና ከሃዲ አይደለም። አልነበረም። ይህን ድርጅት ለማጥፋት ደርግ በነቂስ ገድያለሁ ብሎ እንዳልቻለ ሁሉ። ወያኔም የቻለችውን አድርጋ አልሆነም። ትቂቶችም ቀይ ሽብር ይፈፋም ብለው ግራ እጃቸውን ቀስረው የፈከሩት ዛሬም የገደሉት፣ ያስገደሉት አልያም የገረፉት ወይም ያስገረፉት አልበቃቸው ብሎ ዳግም ያንን ጊዜ ሲመኙ ስናይ፣ ዳግም አንድ ትውልድን የመጨረስ ነውጣቸው ተነስቶባቸው ሲገለገሉ ስንሰማ በሀዘን ነው። ካለፈ ጥፋት መማር ያባት ነው። በጨዋ አነጋገር የጨዋ ሰው ልክ ነው ይባላል። ይህ መከረኛ ድርጅት ታገለ እንጅ አልገደለም። ታሰረ እንጅ ወህኒ ከፍቶ አላጎረም። ተገረፈ፣ ተወገረ እንጅ ወፌ ይላላን ከምስራቅ ጀርመኖች ተምሮ አላንጠለጠለም። ሀ እና ለ በፈጠሩት አንጃ አጋልጹ ተጋለጹ ተብሎ አንድ ትውልድ ታረደ እንጅ አላሳረደም። ይህን ኩነት አለም ያወቀው ጸሀይ የሞቀው እውነት ነው። የቱን ያክል ጥርስ ቢነክሱ እውነትን ቀይረው በቦታዋ አስመሳይዋን ሊያስቀምጡ አይቻላቸውም። አሲምባም ሆነ፣ መቀጣ ውሃ ወይንም ባሕርዳር፣ ሐረርና አዲስ አበባ፣ ወይንም አዋሳ አለያም ናዝሬትን ለምስክርነት ማቆም ይቻላል። ዲሞን በዲሞትፈር፣ ቀይ ሽብር ይፋፋም ብለው የድሐ ልጅን ያረዱባቸው ገበያወች፣ ጎዳናወች አስፋልቱና ኮረኮንቹ ላይ የፈሰሰው ደም አልደረቀም። የነዚያ እናቶች ገሚሶቹ በገመድ ወገባቸውን እንዳሰሩ ዛሬም አሉ፣ ትቂቶቹም እህ ህ እንዳሉ አልፈዋል። ታሪክ ግን ዛሬም ለፍርድ ትጮሐለች፣ የነዚያ እምቦቀቅላ፣ ለግላጋ ወጣት ደምም እንዲሁ።
ጎበዝ እባካችሁ አታፊዙ። ለምን አሁንም ደማችሁ ይሮሯጣል።

መንጋ አገር ገንጣይና አስገንጣይ ሞልቶ ተርፎ በአረዱትና ባሳረዱት ድርጅት ላይ ዳግም ሲፎክሩ ስናይ አሁንም በሐዘን ነው።

በየመንደሩም ሆነ በየጓዳ ጎድጓዳው ገብታ ወያኔ ካልተቆጣጠርሁ እያለችን። ለአመታት የሰራናቸውን አድባራትና፣ ተቋማት በውድ ሳይሆን በግድ ልትነጥቀን እየታገለች ዘወር ብለው ጠላቴ ኢሕአፓ ነው ሲሉን ለጤና አለመሆኑን እንረዳለን፣ ብሎም አንገረምም። ያደቆነ ሰ….ሳያቀሥ አይለቅም ይሉ የለ፧ አላሞዲንን አይነት ቱጃር እንኳን ለሆዱ አደር ሰውን አገር ለመግዛትም ለመሸጥም ይወዋላል።

ለሁሉም አቧራው ይርጋ፣ እኛም ከራሳችን እንሟገት፣ በአገራችን የተንሰራፋውን ዘረኛና ጠባብ ብሔርተኛ ቡድን ለማስወገድ በግንባር ከቆሙት እንተባበር። እናውቃለን የወያኔ መግቢያ ቀዳዳ ብዙ ነውና ሁሉም ወገን ዘብ ይቁም እንላለን።

በዚህ ባለንበት ከተማም እንደያኔው በሰሞኑ መፈክሩ ደርቶ እየተመለከትን ነው። ድርጊቱ ከሰላሳ አምስት አመታት በፊት ትውስታ ቀስቅሶብናል ያኔ አንድ አንካሳ ድርጅት በ1969 ዲሞን በዲሞትፈር ብሎ ነበር። ግማሽ መንገድ ሳይሄድ እሱው በዲሞትፈር ሆነ ይባላል። ወግን ወግ ያነሳዋል። ተረብም ከሆነ መልካም እንላለን። ግን ለምን በሰማእታቱ መተረብ ተከጀለ? መሳቂያ መሳለቂያ ሞልቶ ተርፎ። ኢሕአፓ አይደለሁም ለሚል፣ ወያኔ ይቀርበኛል ለሚል ለምን በሌለበት ይሰየማል (ይታማል)?

አንድ ወዳጀ ደወለና ስማ አለኝ። ነገሩ ግራ ተጋባኝ፣ ስልክ ደውሎ ደህንነቴን ሳይጥይቅ ወይም የእግዜር ሰላምታ ሳይሰጠኝ ሊነግረኝ ወዳሰበው መሄዱ አስገርሞኝ በውስጤ ያ ለዛው የትሄደ? ያሰው አክባሪነት ማን ነጠቀው ዛሬ በሚል በልቦናየ መልስ የለሽ ጥያቄ ውስጥ እንዳለሁ ንግግሩን ቀጠለና የነእንቶኔን መጣጥፍ አየህ የሚል ዳግም ከሰላምታ የቀደመ ጥያቄ ጋር ተፋጠጥሁ። ኢሕአፓ ሳይሆን ኢሕአፓ ያልሆኑት እንዴውም አልማን እንደግፋለን የሚሉት በኢሕአፓ ስም ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው ይለኛል። ነገሩ ግራ ያጋባልና ዛሬ ነገሩ ሁሉ ጠፋብህ ምነው ጃል ባትደባልቅ ስለው። አይ አንተደሞ አትሰማም፤ ዳግም ዲሞን በዲሞትፈር የሚሉ ተነስተዋል ይለኛል። አሁንም ሊገባኝ ቀርቶ ወዳጀን ተጠራጠርሁት። እረ በስማም በል። ነው ከመኝታ ተቀስቅሰህ ይሆን ያቃዠህን ቅጥቃጤ የምታወጋልኝ እለዋለሁ። አለመግባባታችንን ያወቀው ወንድሜ በእውነትም መለስ አለና፤ አይ እስኪ የነእንቶኔን ገጽ ተመልከትና ደውልልኝ በል ይቅርታ መልካም ዋል አለና ስልኩን ዘጋ።

በደቂቃ የተባልሁትን ቦታ ደርሸ እኔም እንደሱው ቅጥቃጤ ሆነብኝ መሰል ሀዘን አይሉት ብስጭት አንድ ነገር ወረረኝ። በትዝታ የነጎድሁት ወደኋላ 35 አመት ይሆናልና እነዚያ ቡቃያወች፣ አንድ ፍሬ ልጆች፣ ለአገር ቀናኢ የነበራቸው ሞትን ላገር፣ ለወገን እድገትና ብልጽግና ሲሉ በፀጋ ተቀብለው አልፈዋል። የሰሜን ተገንጣይና አስገንጣዮች ባንድ በኩል፤ አገር በቀል ጭራቆች በሌላ በኩል ተባብረውና ተጋግዘው ገለዋቸዋል። ጠላቶቻቸው ብዙ ነበሩ፤ አሁንም የነሱ ሞት ያለበቃቸው ምስለኔወች ታሪካቸውን ጨምረው ከምድር ገጽ ሊያጠፉ የሚመኙ ገዳዮች፣ ጠቋሚወች፣ አስገዳዮች ቢኖሩ አንገረምም። ገሚሶቹ በዘርና በክልል ተደራጅተው፣ በልባቸው እንደሰሜኖቹና ሕውሐት ሁሉ ልባቸው ከናት አገራቸው ተነጥሎ ለመሄድ የሸፈተ ነው። እኒህ አይነቶቹ ያው አ.ል.ማ እንዳሉትና የትግራይ ነጻ አውጭ ነን እንደሚሉት ይሉንታ ቢስ ስለሆኑ ያሉትን ቢሉን አንፈርድም። ግን ታጋይን ከባንዳ ባይደባልቁ መልካም ነው እንላለን።

ሌላው አዲስ ክስተት የሌለ ደጃዝማችነት ለራሳቸው የሰጡና እራሳቸውን አንቱ ያሉ በየጊዜው ስለነጻ ምርጫ፣ ስለእኩልነት፣ በብዙሐን ድምስ ስለመገዛት እያወሩን፣ እነሱ ከሌሉበት፣ ወይንም እነሱ ያልባረኩት ሊሆን አይችልም ሲሉ በትዝብት አስተውለናል።፡ ይባስ ብለው አጀንዳ ካላቸው ያላሙዲንና የሕወሐት አጀንዳ ተሸካሚወች ጋር በገሐድ ወግነው ፒቲሽን (Petition) ማስፈረም ሲበቁ ልባችንን ሰብረውታል። ለሁሉም በዚህም ይሁን በዚያ የኢሕአፓ ስም ሲጠራ ዛራቸው የሚወርዱት ሁሉ፣ ሊገነዘቡ የሚገባው አንድ ጥብቅ ነገር አለ። አገር ሻጭ፣ ገንጣይ አስገንጣይ ወይንም ከአንባገነን ጭራቆችም ሆነ ከአድር ባይ እንደገበታ ውሀ ዛሬ ከዚህ ነገ ከወዲያኛው ከሚሉትም ተራ የማይቆም፣ ጽኑ አላማ ያላቸውን ለምንም አይነት ድለላ ወይንም የግል ዝና የማይቆሙ አባላትን ያሰባሰበ የአያሌ ስማእታት ድርጅት ነው። ኢሕአፓን ለቀቅ። አገር አጥፊ አስገንጣይና ገንጣዮችን ጠበቅ። በሰፊው እስክንመለስ በቸር ይግጠመን። 

1 comment:

  1. ውድ ወንድሜ፤

    አብዛኛው ይህ ጽሁፍ የኔ ስለነበር ብትጠቅስ ጥሩ ነው።

    ነገር ግን ከሚያደንቁህ መሀል ነኝ። በርታ። ቀን ያልፋል።

    ReplyDelete