Wednesday, September 29, 2010

እነሱም እኛን ይላሉ፤ እኛም እነሱን እንላለን።

ፖለቲካና ፖለቲከኞች ሲሉና፣ ስንል
ᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

ለውይይት ይሆነን ዘንድ ይህን የተለመደ አባባል አቅርበናል። ይህ ቃል ባገራችን በብዙ የተለመደው ለሰበአዊ መብት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለማነኛውም አይነት እኩልነት ሲሉ ለሚሟገቱ ሁሉ የሚሰጥ ቃል ነው። ብዙሐን ዜጋ ፖለቲካ የሚለውን ጥሬ ቃል ጨርሶ አይጠቀምበትም፣ ወይንም አያውቀውም። አወቅን የሚሉት ቃሉን በአግባቡ አይጠቀሙበትም። በይበልጥም ባገራችን ላለፉት 40 አመታት በተደረገው የሰበአዊ  መብትን፣ እኩልነትን፣ ዴሞክራሲን የማስፈን ትግልና በአንባገነን መንግስቶች የተደረገው ጭፍጨፋ የሕዝብ ልጆችን የበላ በመሆኑ ፖለቲካን ከዚህ የመብት ማስከበር ትግል ጋር በማያያዝ፤ ሰው በላ ጭራቅ አርገው ያቀርቡታል። ይህን የተገነዘቡት አንባገነኖች ግዛትና ስልጣን ለተወሰነ ክፍል የተሰጠ ሌላው ዜጋ ለጥ ሰጥ ብሎ የሚገዛ መሆኑን ለማሳየት የቃሉን አገባብ ለሚቀናቀኗቸው መጠቀሚያ እንዲሆን ይገለገሉበታል። ዛሬ ፖለቲከኛ የሚለው ቃል በስልጣን ላይ ላሉ ጨቋኝ ገዥወች የሚጠቅም ሳይሆን። ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ለሰበአዊ መብት መከበር ለሚታገሉ ሐይሎች የሚሰጥ ማስፈራሪያ ቃል ሆኗል።

ለመሆኑ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው? ቀጥተኛ ቃሉ እንደሚያመለክተው ሕብረተሰብን ሕግንና ደንብን አውጥቶ የሚያገለግል ማለት ነው። ፖለቲካ ስንል ሁሉም በህብረተሰብ ውስጥ ያለ። ከእለት ጉርስና ልብስ ጀምሮ እስከ ማሕከላዊ አስተዳደር ያለው ማለት ነው። ፖለቲካ እንደየአገዛዞች ይለያያል። ከኛ አገር አንባገነኖች በፈረቃ ከሚገለገሉበት አዛዥ፣ ናዛዥ የሆነው ፖለቲካና፤ ዜጎቻቸው በአንድ ማህከላዊ ስርአትና ደንብ ለማንም በማያዳላ ሕገመንግስት ሕዝብ በሚመርጠው የሚተዳደሩ አገራት፤ ያለው ፖለቲካ የሰማይና የምድር ያክል ልዩ ናቸው።ከቃሉ በስተቀር በአፈጻጸምና ተግባራት የሚያገናኛቸው የጋራ የሆነ ምንም ነገር የላቸውም። ፖለቲካ ስሙ አንድ ይሁን እንጅ ከላይ እንደጠቀስነው በሁሉም የህብረተሰብ ክንዋኔወች ስለሚገባ ለምሳሌ፤ የቤተክርስቲያን ፖለቲካ፣ የኮሚውኒቲ ፖለቲካ፣ የዩኒየን ፖለቲካ ወዘተ እያሉ ይጠቀሙበታል። ፖለቲካ በእንዲህ አይነት ትርጓሜው በየስብስቡ ውስጥ ሰወች ሕግና ደንብ አውጥተው የሚተዳደሩበት ማለት መሆኑ ነው። ይህን ወደኛ አገር ብናዞረው። የእድር ፖለቲካ፣ የእቁብ ፖለቲካ፣ የሰንበቴ ፖለቲካ፣ እልፍ ብሎም የብሎግ ፖለቲካ ብንለውም ይቻላል ማለት ነው።

አንዳንድ ጠበብቶች ከምንበላውና ከምንጠጣው ጀምሮ ማነኛውም ነገር ፖለቲካ ተጨምሮበታል ይላሉ። ይህ አበባል በእርግጥም ትክክል ነው። የዩ ኤስ አሜሪካ libertarian አስተሳሰብ ያላቸው ስብስቦችም ሆነ ግለሰቦች ከለዘብተኛ liberal አስተሳሰብ ካላቸው የሚለያቸው አንዱና ዋነኛው ነገር። ለዘብተኞች ሁሉም ነገር ደንብና ድንጋጌ ሊኖረው ይገባል ሲሎ ሊብረተሪያኖቹ ምንም አይነት ድንጋጌ አያስፈልግም ይላሉ። በሁለቱ መካከል ያለው የአስተሳሰብ ልዩነት መንግስት ይኑር በሚልና መንግስት አይኑር በሚሉት (anarchist) መካከል ካለው በትቂት ቢለይ ነው። ሆኖም ሁለቱም አይነት አስተሳሰቦች ፖእለቲካ ናቸው።

አንዳንድ ወገኖች ሁሉን ነገር ፖለቲካ ነው ሲሉ ይደመጣል አበባሉ ትክክል ሆኖ ሳለ ፖለቲካ ማለት እነሱን የማይጨምር አርገው ይወስዱታል። ሌሎች ደግሞ ፖለቲካ አንወድም ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ አባባል በየትኛውም ትርጓሜ ቢሆን ስህተት ይሆናል። ፖለቲካ ማለት ከምንለብሰውና ከምንመገበው ጀምሮ ያለ ነገር ነው ካልን። ፖለቲካና ኤሌክትሪክ በሩቅ፤ ፖለቲካ እንጠላለን የሚሉትን አላወቃችሁም ብንል አልተሰሳትንም ማለት ነው። ምክንያቱም ማንም ሰው ከፖለቲካዊ ድንጋጌወች ውጭ እራሱን ነጻ አድርጎ አያውቅምና። ማነኛውም የእለት ከለት ኑሮና ክንዋኔ ፖለቲካዊ ይዞታ ካለው እንደወፍ ነጻ ነኝ ካልተባለ፤ ከፖለቲካ የራቅን አይደለንም ማለት ነው። በመሰረቱ ፖለቲካ አልወድም፣ ወይንም ፖለቲካና ኤሌትሪክ በሩቅ ማለትም እራሱን የቻለ ፖለቲካ ነው። እንደስብስብ፣ ወይም እንደማሕረሰብ አንዱን ወገን ሌላው እጠላለሁ ማለት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። አንድ አይሪሽ እንግሊዛዊውን እጠላለሁ እንደማለት ይቆጠራል። ወይንም በኛ አገር ወያኔ እንዳመጣብን ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ እንደሚሉት ቃላት ማለት ነው። እነዚህ ቃላት ውስጠ ሚስጥር አላቸው። አንድ ጥቅል ማሕበረሰብን በጅምላ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ ይሉታል። ይህም የጥላቻ ፖለቲካ ይባላል ማለት ነው። ለመሆኑ የፍቅር ፖለቲካ አለ የሚል ጥያቄ እንዳይነሳ እንጅ የሚሆነው መልስ ሁሉም ነገር ይሁን ከተባለ ፖለቲካ ነው ማለት ነዋ።

እዚህ በአሜሪካን አገር እንደምንታዘበው፤ ለምሳሌ ውርጃን የሚቃወሙና የሚደግፉ ሰወች አሉ። ለነገሩ እራሴን አንዱ ባደርግ ከዚህ ውስጥ የሚሰማኝን መናገር እችላለሁ (prochoice,. prolife) ይባላሉ። ሁለቱ ክፍሎች የሰማይና የምድርን ያክል የተራራቀ አመለካከት አላቸው። ታዲያ (abortion) የምትለዋን ቃል ሁለቱም አይጠቀሙባትም። ሁለቱ ቃሎች ወደ አሜሪካ የሕግ ዙሪያም ሆነ በሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲወች ሚና ለይተው በየምርጫው እንደመስፈርት ለሕዝቡ ይቀርባሉ። የእምነት ቤቶች ሳይቀር ተመሳሳይ የሆነ አፈራረጅ አላቸው። (the Christian right movement) የሚባለው የወግ አጥባቂውን ፖለቲካዊ መስመር የሚያራምድ ሲሆን ለዘብተኛ የሆኑ አቢያተ ክርስቲያናትም አሉባቸው። Interfaith dialog, የተለያዩ አማንያንን በአንድ ማህከል ለማስቀመጥና በእምነቶች ተማካኝቶ በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቆም የሚጥሩ፤ መተዋወቅንና መግባባትን እንዲመጣ የሚደክሙ ክፍሎችም አሉበት። ታዲያ እነዚህን መሰል የሐይማኖት ተቋማት ፈጽሞ የማይገናኙ የእምነት ጎራወች ናቸው ማለት ነው። በየሁለት አመቱ ለህግ መወሰኛው ምክር ቤት ምርጫም ሆነ በየአራት አመቱ አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ከላይ የጠቀስናቸው የእምነት ጎራወች ሚና ለይተው በሁለቱ የፖለቲካ ጎራወች ተቧድነው የምረጡን ዘመቻውን በየፊናቸው ያደርጋሉ።

ዛሬ አለምን የሚያምሳት በሐይማኖት ዙሪያ ተሳቦ አንዱ በሌላው ላይ የበላይ ለመሆን። ወይንም ግዛትና ስልጣን ይገባኛል የሚልና፤ አይሆንም በማለት የያዘውን የበላይነት ላለማጣት በሚፍጨረጨረው መካከል የሚደረገው ጦርነት ነው። ላለፉት 70 አመታት በፍልስጤማውያንና በይሁዳውያን መካከል የተደረገው ጦርነት ከዚህ የተለየ አይደለም። ፍልስጤሞችና ይሁዲወች የአንድ ዘር ትውልዶች ሆነው ሳለ የሚለያቸው ሀይማኖቱ ነው። አብሮ ላለመኖርም ይህን ያክል ለገላጋይ አስቸጋሪ የሆነው ግጭታቸው ሐይማኖታዊ ነው ይባላል። ሆኖም ውስጠ ሚስጥሩ አንዱ በሌላው የበላይ ሆኖ ለመግዛት ፖለቲካዊ ፍላጎት ነው። መፍትሄውም አማንያኑ ሐይማኖታቸውን መቀየር ወይንም አንድ ሌላውን ማጥፋት ሳይሆን። ፖለቲካዊ የሆነ መፍትሔ የማግኘት ነው።

ወያኔወች ከ35 አመት በፊት ተደራጅተው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ነፍጠኛ ትምክህተኛ ሰራሽ የመቶ አመት ታሪክ ያላት፤ እሷን ከፋፍለን በቦታዋ የብሔር በሔረሰቦችና ሕዝቦች ፌደሬሽን እንፈጥራልን ማለታቸው። እንደሚሉት አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ጨቋኝ ሌሎች ተጨቋኝ ሆነው አልነበረም። ወይንም ንጹህ በደም ያልተደባለቀ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ ወይንም ከሌሎች ኖሮ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔወችም ሆኑ ሌሎች ክልልተኞች እንደሚሉት ሳይሆን የተገላቢጦሽ፤ አንዱ ከሌላው የተዋለደ፣ ለብዙ ሽህወች አመታት አብሮ የኖረ ነው። ታዲያ እነሱ የበላይ ሆነው ለመግዛት ሲፈልጉ አቋራጩ መንገድ፣ በቀላሉ ለመቀስቀሻ የሚጠቅም ሆኖ በመገኘቱ ተጠቀሙበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በማለት ፈንታ፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ተውጣጣ እንደተሰራች ሁሉ (የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይላሉ) በእጅጉ የከፋው ደግሞ ከፋፍሎ መግዛትን ይሁነኝ ብለው መቀጠላቸው ነው። ይህ ማለት እንግዲህ ወያኔወችም ሆኑ ሌሎች ጎጠኛ አስተሳሰብ ያላቸው፡ ለኔነው ለሚሉት ከልብ ተቆርቁረው ሳይሆን። የተሻለ ቀለል ያለ አማራጭ ነው ብለው ስላመኑና የፖለቲካ የበላይነቱን በከፋፍለህ ግዛው እረጅም የግዛት ዘመን እናገኛለን በማለት ነው። ይህም ፖለቲካ ነው እንዴውም የከፋ የከረፋ ፖለቲካ።

No comments:

Post a Comment