Monday, September 6, 2010

Ethiopian Day 2010

ብንተባበር እንቆማለን፤ ብንለያይ እንወድቃለን
ᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

በዚህ በምንኖርበት አገር ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የመጡ ብዙ ሕዝቦች አሉ። አንዳንዶቹ ቀደም ባለው ዘመን የገቡ ሲሆን ሌሎቹ በቅርብ የመጀመሪያ ትውልድ ናቸው። ቀደም ባለው ዘመን ከገቡትና ከጥቁር አሜሪካውያን ወይንም ከአውሮፓ መጤወች ውጭ የሆኑት ቻይናውያን ሲሆኑ። ከ 1950 ጀምረው መግባት የጀመሩት ሕንዶች፣ ፓኪስታኖችና አረቦች በሚቀጥለው እረድፍ ይገኛሉ። እነዚህ ማሐበረሰቦች አንዳንዶቹ ተቀላቅለውና ተዋህደው ማንነታቸውን ያጡ ሲኖሩባቸው ትቂቶቹ እራሳቸውን አግልለው የራሳቸውን ማሕበረሰብ ሰብሰብ አርገው እንዴውም የዚህን አገር መስራች ነን ከሚሉት የአንግሎ አውሮፓ ዘሮች የሚስተካከል ሐብትና ንብረት መቆጣጠር ጀምረዋል። በዚህ በኩል በመልካም ምሳሌነት የሚታዩት የሩቅ ምስራቅ መጤወች ሲሆኑ። ምንም እንኳን ከኮርያ፣ ቻይና፣ ላኦስ፣ ካቦዲያና ቬትናም ቢመጡም አንድ የሆነ መለያ መያዝ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። እራሳቸውን ከሌላው አግልለው ወይም (segregated) አርገው፤ ማሕበረሰባቸውን ፍላጎት የሚያሟላ የንግድ፣ የግንኙነትና የትምሕርት ተቋማትን መስርተዋል። በመላው የሰሜን አሜሪካ ከተሞችና ክፍለሀገራት Chinatown ተብለው የተሰየሙ ከተሞችን ማየት የተለመደ ነገር ሆኗል። በነዚህ ከተሞች ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ የገበያ አዳራሾች የትራንስፖርትና የጤና አገልግሎት መስጫወች ማየት አዲስ አይደለም። ሌላው አግልሏቸው ሳይሆን እራሳቸውን አግልለው የራሳቸውን ስራና ፍላጎት በራሳቸው ፈጻሚ በመሆናቸው ነው።

አሁን በቅርብ እያደገ የመጣው ሌላው መጤ ኮሚውኒቲ የላቲን መጤወች መንደሮችና ከተሞች በዚህ በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛት በተለየም በቴክሳስ፣ ኒው ሜክሲኮ፣ አሪዞናና ካሊፎርኒያ እየጨመረ መሄድ ነው። እንደ የሩቅ ምስራቅ መጤወች ሁሉ የደቡብ አሜሪካን ላቲን ዘሮች ሜክሲኮወች በሚል መታወቅ ጀምረዋል። ከላይ በተጠቀሱት የአሜሪካ ክፈለ ግዛቶች ዛሬ little Mexico በሚል መጠሪያ የሚታወቁ ከተሞች እድገት እያየን ነው። ላቲኖች በሰፈሩባቸው ከተሞች እንደ እስያውያኑ ሁሉ የራሳቸው የሆኑ ተቋማትን አደራጅተዋል። አዲስ መጥ ዜጎቻቸው አይቸገሩም ማንኛውንም ግልጋሎት በራሳቸው ቋንቋና ባሕል ያገኛሉ። የምናየው ድንበራችን ተጣሰ የሚለው ሁካታ ምክንያቱ ይህ እያደገ ያለ ማሕበረሰብ ወደፊት ሊያመጣ የሚችለውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ሁለንተናዊ ለውጥ በመፍራት ነው። ይህ ማለት በዚህች አገር በንብረት የጠነከረ፣ የመምረጥ የመመረጥ ቁጥር ያለው ሁሉ የወሳኝነት ሀይል ስለሚፈጥር፣ ቀድመው የሰፈሩትን የአውሮፓውያንን የበላይነት ያዳክማል ከሚልም ስጋት ለመሆኑ ይገመታል። ያም ሆነ ይህ አድ አይነት ባህል፣ ቋንቋና ቀለም ያላቸው አብሮ መኖርን ሲጀምሩ ከአብሮ መኖር ጋር ሊከተሉ የሚገባቸውን የራስ የሆኑ በራስ የሚተዳደሩ ተቋማትን፤ የንግድም ሆነ ማነኛውም ማሳደግ ምንም አይነት ጉዳት የሌለው ጠቀሜታው ግን በግል እንደሚታየው መከበርን፣ የራስ ማህበረሰብን መጥቀምና ማሳደግን፤ ከብልጽግና ጋር አዋህዶ ያመጣል።

የኢትዮጵያ ኮሚውኒቲ በሰሜን አሜሪካ

እኛ በስደተኝነት መውጣት ከጀመርን ምናልባት ከ35 አመት የማይበልጥ ጊዜ ነው። ብዙወች የመጀመሪያ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ማሕከላዊ እድሜ ከ55 60 ይደርሳል። ለአለፉት ስድስትና ሰባት አመታት እዚህ ተወልደው ያደጉ ልጆቻችን የከፍተኛ ትምህርት መግባትና ትቂቶችም መጨረስን አይተናል። አንጻራዊ በሆነ መልኩ ኢትዮጵያውያን በተለየና አፍሪካውያን አዲስ መጭወች በጥቅል መልካም ሁኔታ ላይ ነን። የዩናትድ ስቴትስ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ 2006 እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያውያን በቁጥር ከናይጀሪያና ግብጽ ቀጥለን ሲሆን፣ በስራ ላይ የተሰማራው 84% እንደሆነ ሲያሳይ 42% የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙ ናቸው ይህ አሃዝ ጠንካራ ከሚባለው የእሩቅ ምስራቅ መጤወች በ3% ይበልጣል። ሁለተኛ ትውልዶች ማለትም እኛ የወለድናቸው የእስታትስቲክስ ቁጥር ቢታይ የመጀመሪያ ዲግሪ በመያዝም ሆነ ገና በከፍተኛ ትምህርት ላይ ያሉ ከፍ ያለ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ያም ሆነ ይህ ቻይናውያንና ላቲኖች በራሳቸው ማህበረሰብ መጠቀምንና መጥቀምን ስናይ በኛ በኩል ያለውና የሚታየው ድክመት በእጅጉ የሚያሳስብ ነው ማለት ይቻላል።

አንጻራዊ በሆነ መልኩ ከመላ የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች የቶሮንቶ ኢትዮጵያውያንና በችካጎ የሚኖሩ ዜጎች መደራጀትን በማሳየት የመጀመሪያና ብቸኛ ሆነዋል። እንደሚታወቀው በየትኛውም ከተማ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት የኮሚውኒቲ ማህበራት ተፈጥረዋል። በያሉበት ከተሞች ማግኘትና መስጠት የሚችሉትን አርገዋል ተብሎ አይገመትም። ለምሳሌ የራስ የሆነ ማህከል፣ የጤናም ሆነ ማህበራዊ ወይንም የንግድ አላሳደጉም። ከመንግስት ሊገኝ የሚችሉ ግልጋሎቶችን በመደራጀት አልተገኙም። በአኖኗርም ቢሆን ተበትነው ይኖራሉ። ይህንና የመሳሰሉ አንድ ማህበረሰብ ሊኖረው ወይም ሊፈጽመው የሚገቡ ተግባራት በኛ በኢትዮጵያውያን አልተፈጸሙም ማለት ነው። ይህ ወደፊት ተተኪወችን ሊጎዳ ይችላል። ልጆቻችን ከኛ ተረክበው አገራቸውን፣ ማንነታቸውን አውቀውና ተገንዝበው የጋራ ኑሮን፣ ትብብርንና የጋራ ጥንካሬን እንዳይረከቡ ያረጋል ማለት ነው።

ወደዚህ ወደዳላስ ስንዞር ኮሚውኒታችን ከተመሰረተ 26 አመታት አልፎታል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እድገት እየታየ ቢሆንም። ታየ የተባለው እድገት አሁንም ቢሆን አንድ ማሕከል መፍጠር አልቻለም። ከስምንት አመታት በፊት በ አቶ ይልማ ፈለቀ፣ በአቶ ይልማ ዘሪሁን፣ አቶ ግርማ ንጉሴ፣ ው/ሮ ምስራቅ ጣሰው፣ ው/ሮ ቀጸላ ከበደ አቶ ሙስጦፋ በሽር የተጀመረው የኢትዮጵያ ቀን አንድ መልካም ስራ መሆኑን ግን አሁንም ማወቅ ይገባል። ከዚያም በፊት በአቶ ሚዲቅሳ፣ አቶ ሰለሞን፣ እንዲሁም በአቶ ሰይፉ ታደሰ የተጀመረው የኮሚውኒቲ ሬዲዮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በቅርቡ የተጀመረው የእድር ማሕበር እያበረከተ ያለውን አስተዋጸኦ መናቅ አይቻልም። ከላይ የዘረዘርናቸው መልካም ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው የአንድ ጎልማሳ እድሜ ያስቆጠረ ድርጅት የበለጠ ማድረግ ይችል እንደነበር ግን መሳትም አይገባም። ከላይ እንደታየው ሌሎች ማሕበረሰቦች ተደራጅተው ያገኙትን ጥቅምና የሰጡትን ግልጋሎት እኛም ማግኘት እንችል ነበር። ይህ ሳይሆን ብዙ አመታት ተቆጥረዋል። ሌላው የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ነው። ብዙ ወገኖች የጋራነትን ጥቅም አልተረዱም ወይንም ኮሚውኒቲ ማሕበሩ አላወቀበትም። በብዙ ሽህ የሚቆጠር ሕዝብ በሚኖርበት ከተማ በጣት የሚቆጠሩ ሰወች ብቻ አባል መሆን ችግሩ ከየት ለመሆኑ መረዳት ይኖርብናል። ባንድ ወቅት ይህ ማሕበር ጨርሶ ዳብዛው ሊጠፋ እንደነበር ማስታወስ ይገባል።፡ ወደፊትም በዚህ ማህበር አመራር ለማገልገል የሚፈልጉም ሆኑ የተመረጡ ወገኖች ለእድገቱ ዘዴ መፈለግ ይጠበቅባቸዋል። ከሌሎችም ከተለያዩ ኮሚውኒቲወች፤ ከሕንዶች፣ ከቬትናምና በጠቅላላ ከሩቅ ምስራቅ ሰወች ልምድን ማግኘት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ብዙወች ውጤት አምጥተዋል። የራስ የሚሉት ተቋማትንም ሆነ ንብረት አፍርተዋል። እኛ በቁጥርም ሆነ በሌላው ሁሉ ብቃት ያለን ስልሆን የአካሄድ መላውን ከተማርን ተመሳሳይ ውጤት ልናመጣ እንችላለን። በተጨማሪ ከራሳችን ወገኖች ችካጎና ቶሮንቶ ልንማረው የምንችለው ብዙ ይኖራል። መሪወችንም ስንመርጥ ሆነ ለመመረጥ የሚቀርቡ እጩወች አንድም በሐይማኖት ፣ በቋንቋ፣ በጾታ ስብጥራቸው ሁለትም ይህን ኮሚውኒቲ መለወጥ እችላለሁ ብለው ያመኑና ሊሰሩ የተነሳሱ መሆን ይገባል። ኮሚውኒቲው ቢያድግ ተግባራቱን እንዲፈጽሙ የሚመረጡም ለልፋታቸውም ሆነ ለሚያጠፉት የግልጋሎት ሰአታት በተደጎሙ። በሌሎች ከተሞችና በሌሎች ኮሚውኒቲወች እንደሚደረገው ማለት ነው። ሌላው ኮሚውኒቲ ማህበሩ ሊያድግ የሚችለው ከልብ ድጋፍ ሲያገኝ መሆኑን ማወቅ ለዚያም የመላ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ መሻት። በተለየም በዚህ ባለንበት ከተማ ብዙ በሰብአዊነት በግል ወገን የሚረዱ ዜጎች አሉ። እነኝህ ወገኖች ተመረጡም አልተመረጡ ሰብአዊ ድጋፋቸውን ለግለሰቦች ያደርጋሉ። ከነሱ ጋር መስራት፣ እነሱን ማቅረብም ይገባል። መልካምና አዋቂ መሪወችም እንዲኖሩት ሲታሰብ እንዲሁ የሁላችንም ተሳትፎ ሲጨመርበት መሆኑን አለመርሳት ያስፈልጋል። ይህ ማለት አሁን ያሉት መሪወቹም ሆነ ከዚህ ቀደም የነበሩት አዋቂና ብቁ አይደሉም ማለት አይደለም። እኔ እስከማውቀው ወገን የሚወዱ ጠንካራ ወንድሞችና እህቶች እንዳሉበት ነው። ሆኖም አሁንም ከታሰበ አመታት ያስቆጠረው ማህከል እውን ባለመሆኑ ስሜታችንን የሚቆጠቁጠን ብዞወች እንዳለን ሊታወቅ ይገባል።

ለሁሉም ዛሬ ለዚህ የኢትዮጵያ ቀን እንኳን አደረሰን። ብንተባበር ለውጥ ማምጣት እንችላለን። ስንተራረብ፣ ስንገፋፋና ስንጋጭ ለውጡም ፍቅሩም እደገቱም አብረው ይጠፋሉ።

ሌላው በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅሰው የማላልፈው በሰሞኑ የታየን አንድ አጋጣሚ ነው። የወይዘሪት ብርቱካን ሚዲቅሳን በግፍ መታሰርና ያለፍርድና ባልሰራችው ወንጀል በዘረኞች መንግስት ተወንጅላ ላለፉት ሁለት አመታት በእስር ላይ መሆን አስመልክቶ ደጋፊወች ገንዘባቸውን ከፍለው ድንኳን ለመትከልና የሷንና ሌሎችን በግፈኞች መንግስት መጋዝን አስመልክቶ የኢትዮጵያን ቀን ለመካፈል ለሚመጡ ወገኖችም ሆነ የውጭ ዜጎች ለማሳየት ታስቦ የተጠየቀውን ቦታ አንድ ለጊዜው ስሙን መጥቀስ የማይገባ ግለሰብ ለመከልከል አስቦና ተከራክሮ በሌሎች የኮሚውኒቲው አመራሮች በመፈቀዱ፤ ይህን ሰባዊነት ለደገፉ ምስጋና፤ ያነን ሰብአዊነት ለመንፈግ የአሳሪወች ተባባሪ በማወቅ ወይንም ባለማወቅ የሆነውን ግለሰብ በሐዘኔታ ሳልጠቁም ማለፍ ይከብዳል። እዚህ ላይ ሁሉ ነገር ፖለቲካ ነው እያሉ የፖለቲካ ውጋኖ የሚሰጡ ወገኖች የፖለቲካን ምንነት እንዲረዱ ቢያስቡ መልካም ነበር። ቸር ይግጠመን።

1 comment:

  1. ... the face value of the article = respect, educational, mature, open and wide heart, and 'good Etiopiyawi Zega'.

    Stick with your current flow.

    Good article.

    ReplyDelete