Wednesday, September 22, 2010

You can't depend on your eyes when your imagination is out of focus, Mark Twain

ግራ ቀኝ ያለማየት ችግር፤ የሚያስከትለው ጉዳት
ᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

መረዋ በተባለ ብሎግ የሚያስነብበን መልካም ጽሁፎች እንደተጠበቁ ሆነው። ጸሐፊውም ሆነ ባልደረቦቻቸው ለሁሉም አይነት የህብረተሰብ ክፍል ያላቸውን ጥላቻ የሚያንጸባርቁ መጣጥፎች ያለማቋረጥ ማቅረቡ ውብና ለዛ ሊኖረው የሚችለውን አበርክⶆአቸውን ሊያደበዝዝ ይችላል። ስለመብት እየተናገሩ የሌሎችን መደራጀት፣ መቃወም አልያም ማጣጣል፤ ይሁነኝ ብለው የተቃዋሚወችን ማናናቅ፤ አንድየ የሆነውን የእምነት ቤት ፍርድቤት አቅርቦ የመብት ማስከበር ትግል ነው ብሎ መፈጸም፤ ጉዞው ወዴት እንደሁ ለምናውቅ ብዙም አይደንቀንም።

ይህ ብሎግ በአንድ ነገር ላይ ብቻ አተኩሮ የቸከ ተደጋጋሚ እሰጥ አገባ ውስጥ ለመግባት ፍላጎቱም ሆነ እምነቱ አይደለም። የሐይማኖት ስራትን የሚያውቁ ሊቃውንት በጉዳዩ ቢሳተፉም የሚሻል እንደሆነም በጥብቅ እናምናለን። ተቋሙ መበደሉን እያየን ገለልተኛ ለመሆን በፍጹ አይቻለንም። ይህን የእምነት ቤት ለመስራት የእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን ሳይቀር ተሳትፈዋልና። የሆነው ሆኖ ግን የማይሆን ነገር ስናይ በዝምታ ልናል አይቻለንም። ቅዳሜ ሴብተምበር 18/2010 በመረዋ ብሎግ ጸሐፊ የተንጸባረቀውን ለመመልከት እና መስመር እንዲይዝ ለመጠየቅ ተገድእናል።

ግለሰቡ የከሳሽን ወገን እንደ ተበዳይ፣ መብቱን እንደተነፈገ አድርገው ለማቅረብ በተደጋጋሚ በሚወጡ መጣጥፎች በዝምታ የሚከታተለውን ወገን ለማስጨበጥ ሞክረዋል። ሌላው “ልጅ ለናቷ ምጥ አስተማረች” እንዲሉ ተሰደብን የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ያነሱታል። እዚህ ላይ ማንም እንዲገነዘብ የምንፈልገው ጉዳይ ይህ ጸሐፊም ሆነ ብሎጉ፤ ወገንን ከማንቋሸሽ ውጤት፣ ስምምነት ይፈጠራል። ወይንም መልካም ነገር ይፈጠራል ብለን አናምንም። ካልተሰሳትን መረዋ ሲጀምር የስድብ ውርጅብኝ በአንድ ቤተሰብ ላይ እንዳወረደ ግን መዘንጋት አይቻልም። ይህ አሁንም ለግንዛቤ እንዲቀመጥ ያስፈልጋል። የሆነው ሆኖ ያም ጸያፍነቱ ታውቆ አሁን በተያዘው መልክ ለመቀጠል የቁርጥ እምነት ከሆነ እሰየው እንላለን። ሆኖም በድጋሜ ለግንዛቤ ሆነ ለመተዛዘብ እንዲሆን በዶክተር ግርማና በቤተሰብ የወረደውን የስድብ ውርጅብኝ ዘሎ እራስን ከዚያ ንጹህ ነን ለማለት መሞከሩ አግባብ የለውም እያልን። ብሎጉ በያዘው እንዲቀጥል አበጀህ እንላለን። ከላይ የጠቀስሁትን ተግባር ዳግም ላለመመለስ ለራስ ማሐላ ገብቶ ለክርክርም፣ ለውይይትም መቀጠሉ አንድ እርምጃ ነው።

በስነ ጽሁፍም ሆነ በትችት አለም። ማንም ተች ወይም ጽሁፍ አቅራቢ ወይንም ተከራካሪ በያዘው አጀንዳ ላይ አስቀድሞ ስለሚጽፈው ጉዳይ እውነትነት ሊያስጨብጥ ይገባል።፡ይህ እውነትነት የሚገኘው እመኑኝ ወይም በምሐላና በመገዘት ሳይሆን የጽሁፉ፣ ትችቱ፣አለያም መከራከሪያው ምንጭ ሲኖረውና በማንም አንባቢ ሊገናዘብ የሚያስችል ማመሳከሪያ ሲቀርብ ነው። አለበለዚያ ድሮ እንደምናውቀው ተራ ፕሮፓጋንዳ ወይንም ያው ዞሮ ስድብ ከመሆን አይዘልም። ለምሳሌ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በመረዋ በኩል ፖለቲካዊ ግፊት አለ ብሎ ያምናል። ይህንም በማስረጃ ለማቅረብ ይቻለዋል። በአቶ ሙሌ ታረቀኝ ከአኢትዮጵያ የወያኔ ኤምባሲ ዲሲ የመጣ ሰው በጠራው የአማራ ልማት ማሕበር (አ.ል.ማ) በተባለ ስብሰባ ቅዳሜ ኤፕሪል 24/2010 በዳላስ መደረጉን “በትኩረት ፮” ኢትዮሚዲያና በሌሎች ድሕረ ገጾች በወጣ ሪፖርታዥ መረዳት ችለናል። በዚያ ስብሰባ ላይ ያሁኖቹ ቤተክርስቲያኑን ፍርድ ቤት አቅራቢወች ተገኝተው የሚገባ ድርሻቸውን በሀሳብም በቁሳቁስም አበርክተዋል። ይህ ስብሰባ በተካሄደ ሳምንት እሁድ ሜይ 2/2010 በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቅድመዝግጅት የተደረገበት፣ በእርግጥም የቪዲዮ ቀራጮች ተዘጋጅተው ሁላችንም እንደታዘብነው በ ቻናል 4 የምሽት ዜና ሆኖ የቀረበውን ገመና ገላጭ የሆነውን ምስል በሁካታው ሲቀረጽ እንደነበር ሁሉም ያውቃል። ይህ ከላይ የጠቀስነው እንደተጠበቀ ሆኖ የዚህ የመረዋ ብሎግ ጸሐፊ ደጋግመው ስለፖለቲካ በተለየም በውጭ የመለስን/ወያኔ አስተዳደር ይቃወማሉ በሚሉት ተቃዋሚ ለማላከክ መከራቸውን ሲያዩ ታዝበናል። የራስ ስራና ተግባርን ለሌሎች ለምን መስጠት አስፈለገ፧ ጥያቄአችን ነው። እንደእውነት ከሆነ የዚያ ብሎግ ጸሐፊ መንግስትን በሲቃ ይደግፋሉ። ይህም መብት ነውና ባልከፋ። ለምን ተናገራችሁብኝ ብለው ይጨነቃሉ። ይህም ሰው የሚወደውን፣ የሚጨነቅ፣ የሚጠበብለትን አትንኩ ማለቱ ነውርነት የለውም። ሆኖም ዞረው ተመልሰው የሚወዱትን እቃ (ወያኔን) ተናገሩት በሚሉት ወገኖች ላይ ያላግባብ የቃላት ክስ ያቀርባሉ። ደግነቱ የመናገር ነጻነት ያለበት አገር መሆኑ። ከሳሽ በተከሳሽ ላይ ማስረጃ ማቅረብ የሚገደድበትም ህገመንግስታዊ አገር በመኖራችን እንጅ። አገርቤት ሆነን ቢሆን (በአ.ል.ማ) በኩል ይቃወማሉ በተባሉት ወገኖች ላይ እንደወንድማችን አካሄድና አረማመድ ቢሆን ከትልቁ ይሙት በቃ ፍርድ ለማሳነስ የግምት መዛባት ይሆን ነበር። ጸሀፊው በሰሞኑ በቁጥር ፵፫ መጣጥፍ እርስ በራሱ የሚጋጭ ሀሳቦችን አስነብበውናል።

በሜይ ፪ ቀን እሁድ ከቅዳሴ በኋላ ስለነበረው ሁከት አስመልክተው ቤተክርስቲያን ፖሊስ እንዴት ሊመጣ ተፈቀደ በሚል ከዚህ በታች ያለውን ይላሉ።

ታዲያ በአሁኑ ሰዓት በአንድ ወገን  በጥቂት የቤተክርስቲያን አመራር ክፍልና በጣት በሚቆጠሩ ደጋፊዋቻቸው በአንጻሩ መብታችንን አናስደፍርም በካህን ታጅበን እንጂ በፖሊስ ተከበን አናመልክም በሚሉ ምእመናን መካከል የተጀመረውን መተናነቅ ስናስተውል  እውነትም ፈተናው አስከፊ እንደሆነ ታየን።
ከላይ በተጠቀሰው አባባል። ብዙ ደካማ እናቶችና አባቶች፤ ሕጻናትን ጨምሮ ባሉበት ቦታ ስርአት አልባ ግርግር ቢነሳና ጉዳት ቢደርስ ማን ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፧ የሚለውን ብንዘል። ለምንስ ጉዳት እስኪደርስ ይጠበቃል የሚሉ ወገኖችን ሐሳብስ እንዴት ድጦና አሳንሶ ማየት ይቻላል። የጸሐፊውን አባባል ሙሉ በሙሉ እጋራለሁ ልበል ምክንያቱም እኛው በእኛ መፍታት የሚቻለውን ለምን ከውጭ ሐይል አመጡ የሚለውን አባባል ማለት ነው። ሆኖም እንዳየነው የተነሳው ሁካታ ቢቀጥልና ገላጋይ የጸጥታ ክፍል ባይኖር አማራጩ ምን ሊሆን ይችል ነበር ብሎ መጠየቅ የሚገባ ይመስለኛል። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የቤተክርስቲያኑን አስተዳደር ከመተችቱ በፊት የነበረውን ሁናቴ ለምን ብሎ ጠይቆ መልስ ተሰጥቶት ሁለት ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተግባሩን በተጨባጭ ተመልክቷልና። በአንጻሩ የመረዋው ትችት አቅራቢ በጊአዜ በማናውቀው ጉዳይ ይህ ድርጊት ሲፈጠርም ሆነ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከጸሎት በኋላ በነበረው ግርግር ከውጭ ቆመው እንደነበር ግን እራሳቸውም ቢሆን ሀሰት እንደማይሉ እገምታለሁ።

መብታችንን አናስደፍረም በሚሉ ምእመናን እና በትቂት የቤተክርስቲያን ደጋፊወች መካከከል የሚለው ይህ በዚህ ጸሐፊ በተሰመረበት ቃል ለአፍታ እንተች። የመረዋው ትችት እንበለው ክስ፣ አቅራቢ። መብት የምትለዋን ቃል ደጋግመው ይጠቀሙባታልና ትርጉሙ ከቤተክርስቲያኑ ጋር እንዴት እንደሚታይ ስላልገባን ለመጠየቅ ተገደናል። ምናልባት ይህን በሚቀጥለው መጣጥፋቸው ያቀርቡታል ብለንም እንገምታለን። ሆኖም እንደሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ከተከፈተ ከ24 አመታት በላይ ነው። በዚህ ባሳለፍናቸው አመታት ሁሉ በስህተትም ይሁን ተዘሎ በግል የተዳደረበት ወይም ያለ አባላት ፈቃድ ግለሰብ የቤተክርስቲያኑን ደንብ ተላልፎ እኔብቻ ያለበት ጊዜ የለም። አባላት መርጠው ያስቀመጧቸው የቦርድ አባላት በፈረቃ አገልግሎት ሰጠዋል። አሁንም በተመሳሳይ የመታዳደሪያ ደንቡን በተደገፈ ተመርጠው የሚያስተዳደሩ ወገኖች አሉ። እነዚህ አደረጉ የሚባለውን ከህግና ደንባችን ውጭ የሰሩትን ማቅረብ ተገቢ ሆኖ ሳለ የወያኔው መለስ “የአይን ቅንድባቸው ካላማረንም እናባርራለን” እንዳለው። እኔና ጓደኞቸ ስለማንወዳቸው፣ ወይንም አቡነ ጳውሎስን ስላልተቀበሉልን፣ ወይንም በሕግና ደንብ ተመርኩዘው ስለቆሙ። የኛን መብት ተጋፍተዋል ካልሆነ። መብታችን የሚባለውን ቃላት በተግባር ቢያሳዩን ተባባሪ በሆንና አብረን በጮህን መልካም ነው እንላለን። ሌላው ለግንዛቤ ያክል፤ አንባ ገነንነት እስከምናውቀው ባገራችን በወያኔው መለስና በሹመኞች በአባ ጳውሎስ እንጅ በየጊዜው በሚመረጥ ቦርድ ይኖራል ለማለት፣ ለዚያም ማገናዘቢያ ለማቅረብ ትንሽ የሚከብድ ቃል ይመስለናል። “ቃል” ያልነው በተግባር ከጥላቻ ያልዘለለ እውነትነት የሌለው ክስ ለማለት ነው።

ከላይ የመረዋው ጸሐፊ ቦርዱ ለምን ፖሊስ አመጣ ብለው እንዳልተከራከሩ ወይም እንዳልጻፉ ወረድ ብለው እንዲህ ይሉናል

እኛ ይህንን ገምግመን መስቀል ካልገዛው ሕግ ይዳኘው ብለው የተነሱትን ደግፈናል።
አንባብያን ግንዛቤ እንዲያገኙ እስኪ ለምን ፖሊስ ጠሩ ብሎ መመጻደቅና አንድ ክስ ሳይዘጋ በእምነት ቤት ያውም በጋራ የገዛነው። በህግና ደንብ በሚተዳደር። የውስጥ መተዳደሪያ ባለው። በየጊዜው የሚፈራረቁ ተመራጭ አስተዳዳሪወች ባሉበት ቤት ለምን ብለው ለሁለተኛ ክስ እንደሄዱ ግን በትክክል ገልጸውት አያውቁም። በዚህ ጸሀፊ እምነት፤ የጋራ የእምነት ቤትን መክሰስ አግባብ ያልሆነ አፍራሽ ተግባር ብሎ ያምናል። የፖሊስ መምጣትን የተቃወመ ሳይውል ሳያድር ፍርድቤት ሄዶ መጥሪያ ይዞ ሲመጣ ስናይ አዝነናል። እንደወያኔው መሪ እሳቸውም ቅንድባቸው የማያምር የሚጠሏቸው ቢኖሩ አንድም ከማያዩበት መሄድ አልያም እንዲለቁላቸው ግለሰቦችን መጠየቅ ከፍርድ ቤት ጉዞ በእጅጉ የተሻለ ነው የሚል እምነት የዚህ ጸሀፊ አቋም ነው።

ፖሊስ አመጡብን ብሎ አናውሮ የተናገረ ጸሀፊ፡ በዚያ ገጽ እኛም ፍርድቤት ሄድን ማለት ትርጉሙ አይገባንም። ወይም በአንድ ስብእና ሁለት የሰውነት ባሕርይ ካልሆነ።

የኛ ችግር በመብት እረገጣ ላይ ነውና ለዚህ ደግሞ ከሕግ ውጭ መፍትሄ ይኖራል ብለን አናምንም።
ይህ አበባል ግልጽ ነው። ቅዱስ ሚካኤል ከሩሲያውያን ደባልነት ወጥተን ኪንግ መንገድ ላይ የነበረውን ስንገዛ። በቅድሚያ ለዚያ ያደረሱን ገለሰቦች እንደነ አቶ ኪዳኔ ምስክር፣ እቶ ሰይፉ ይገዙ ጊዜና ገንዘባቸውን ለግሰው ለዚህ ያበቁን ምስጋና ይድረሳቸውና። እንዲሁም ያለመታከት በአንድ ሆብሎ የቆመው ምእመናንና ሌሎች ስማቸውን ያልጠቀስን ወገኖች ትብብር ለዘላለም ይኑር እያልን። ምናልባት የመረዋው ጸሐፊም አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ። አላስታውስም። ከዚያ ጊዜ እስከአለንበት፤ ቤተክርስቲያናችን ፍርድቤት እስከቀረበበት ድረስ፤ ምንም ችግር አልነበረም ማለት አይቻልም። አለመግባባቶች ነበሩ። ሆኖም በውይይት የሚፈቱት በመልክ በመልኩ ቀርበው ሲያሻ ሽማግሌ አልያም ተወቃቅሶ እንደኖረ ግን ግልጽ ጉዳይ ነው። የፍርድቤት ነገር ከተጀመረ ወዲህ መፍትሄው እሱ ብቻ ብለው የቆሙ ምእመናን በማወቅ ወይንም ባለማወቅ እስካሁን እንዳሉ እናውቃለን። ያነን የመጀመሪያ ፍርድቤት ጉዳይ አገባደን ለሌላ ስንቀርብ ግን። ለምን የሚል ጥያቄ ማጫሩ አልቀረም። ይህን በአንድ በማያወላዳ ስንኝ ልዝጋው። ፍርድቤት መሔድ ዳግም ለማናችንም አያዋጣም። ፍርድቤት መሄድ ለሁላችንም በደል ነው። ማሕበራዊ ትሥስራችንን ያናጋል። ሰላምንና ፍቅርን ያርቃል። በቦታው ማንም ያሸንፍ የመጨረሻ ውጤቱ አንዱን አግላይ ነው ባይ ነን። አሁንም ዳግም ልንረዳው የተቸገርነው ምርጫ ባለበት ቤት የመብት መገፋት የሚለውን ቃል ነው። ይህን ቃል በመልኩ ቢያስረዱን ዳግም እንጠይቃለን። እስከፍርድቤት በምስክር ቃልነት የቀረበ በመሆኑ ማለት ነው።

ወረድ ብለው ጸሐፊው እንዲህ ይላሉ።

አገር ቤት ያልተሳካ ፖለቲካ ዳላስ ያለውን ምእመን በማመስ በለስ ሊቀናን ይችል ይሆናል ብሎ  ማለም ደግሞ በፖለቲካ አለመብሰል ይመስለናል።

ይህ የጸሐፊው አባባል ለሁሉም ችግራችን ማሰሪያ ነው ይላሉ አንዳንድ ወገኖች። ጸሐፊው ስለቦርድ አንባ ገነንነት (በየሁለት አመቱ ስለሚመረጥ አካል) እያወሩ የመጨረሻ ዋና የጽሁፋቸው ማሰሪያ ስንኝ ይህ ከላይ የተቀመጠው ነው። ምናልባት እሳቸው የሚደግፉት ክፍል አሁንም 99.6% አሸናፊ ነኝ ብሎ ስልጣኑን ከያዘና  ሀያ አመታት እየገደለ ተቃዋሚን እያሰረ ገዝቶም ስላልበቃው ፍጹም አንባ ገነንነቱን ድፍን ኢትዮጵያ መረጠኝ በማለት የመቶ አመት ስራውን ቀጥሏል። ያልተሳካ ብለው የሚሳለቁበት ነገር ይህ ሆኖ። ጉልበተኛ በሕዝባችን ጫንቃ ተቀምጦ አናሳወች ጠበንጃ አስካለን ማንም አይነካን እያሉ በሚፎክሩበት አገር በእርግጥም ጸሐፊው ያልተሳካ የሚሉት ስላቃቸው ይህ መሆኑ ነው። ፍርድቤት ለመሄዳቸው ውስጠ ሚስጥርም የሚያፈቅሩትን መንግስት ይቃወማሉ የሚሏቸው ወገኖችን ለማስወገድ። ወይን ከአይናቸው እንዲርቁ ለማድረግ የተረገዘ ተቃዋሚን አልይህ የማለት ጥላቻ ነው ይላሉ አንዳንድ የተማረሩ ወገኖች። እንደአገር ቤቱ እኛ የ አ.ል.ማ አባላት ያለምርጫ ካልያዝነው የሚል ውስጠ ሚስጥር ነው የሚሉም አልታጡም።

ለማጠቃለል፦ የሚቻል ከሆነ አንባ ገነንነት እንዴት በቤተክርስቲያን እንደተፈጠረ። በይበልጥም ተመርጠው የማስተዳደሩን ቦታ በሚይዙ ሊሰራ እንደቻለ ብናይ።

በይበልጥም እምነትን ከግል የማሕበራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ጋር መጨመር አደጋ እንዳለው መገንዘብ።

ከይሆናልና ከጥርጣሬ ወጥተን ጭብጥ ያለው፤ በማስረጃ የተደገፈ ክንዋኔን ቢቀርብ።

ይጠሉኛል፣ ወይንም ይቃወሙኛል ብሎ ማሰብ ከወዲሁ የፍርሐትና ጥርጣሬ ግድግዳ መገድገድ ሲሆን፤ ለማነኛውም አይነት ስልጡን ውይይት መላወሻ ነስቶ አይንህ ላፈር የሚያሰኘውን የጥላቻ ጅረት ለመዝጋት ወደራስ መመልከት።

ከሁሉም በላይ ስለመንፈሳዊነት ከተነጋገርን፤ ከአንድ ወጥ ጎዳና ወጥተን ግራቀኝ እንድናይ እራስን መምከር። በማለት እንጨርሳለን። የነገ ሰው ይበለን። 

2 comments:

  1. “ሲንዶስ”ም በወያኔ፤
    “ሰንበቴ”ውም በወያኔ፤ በአቡነ ጳወሎስ፤
    “ዳላስ-ኢቲኦሲ” በወያኔ፤ በአቡነጳውሎስ፤ በኢ.ኮሚኒቲ፤ …. የማያዋጣ “ክተት ሠራዊት” ይመስለኛል።
    …..
    ዛሬ ደግሞ ኢትዮ.. በበጎ መጓዝ ሲችል (እንዳጀማመሩ) ካላይ እንደብዞዎቹ በቆሙበት ማለትም / “በተጋዳይ” / “በትንሽ” ክፍል አዕምሮ መጓዝ ለምን? ወይስ አካባቢው ሰላም ሆኖ፤ ነፃ ፎረም - ነፃ ፓል ቶክ - ነፃ የውይይት መድረክ ለመፍጠር? …. ስራ ምፍታት!

    የእናትና፤ የባለቤቶቻችንን፤ ዕንባ ማድረቅ ሲቻልል? --- ትናንሽ ሕፃናት ልጆቻችንን በበጎ “ማታለል” ሲቻል?
    ዳግም ወደ ኋላ ለምን!? …

    አዎ ለዚህ ብሎግ ጸሀፊ/ዎች 100፤ 200፤ 300 ሰው ከ1000 ወይም ከ2000 የቤ/ክ መዕምን ውስጥ ብዙ ፋይዳ የሌለው ብሎም በዳይና “መካስ” ያለበት ስብስብ ሆኖ ይሆናልና፤ የሚሻለው ዝምምምምምም. …….

    አይ የሀገሬ ፖለቲካ/ከኞች !.....
    አላማን ለወደቁት! ለተሰዉት! ጀግኖች አባቶች፤ ጀግኖች እናቶች፤ ጀግኖች ወንድሞች እህቶች፤ ብቻ እንዴት እናስብል …. እንዴትስ በነሱ አይን እኛ እንመሰል?.... ያ፤ለነው ትውልድ

    ለአንድ “መረዋ” ሳይሆን ለአንድ እናት ሀዘን፤ አልያም ለህፃናት እንባ ብዕሩ ቢሾል ምንኛ በከበረ!! …
    አዎ፤ የከበሩ ብዕሮች፤ የከበሩ ስነ-ጽሁፋቸው ሁሌም ይዘከሩ!

    ReplyDelete
  2. በእርግጥም በትልቁ ጉዳይ ብንወያይ መልካም ነበር። የዚህ ብሎግ መንፈስና አላማም በቀጣይ ችግር ይኸውም አገርንና ወገንን አስመልክቶ ባለ ጉዳይ ለመወያየት የተመሰረተ ነው። ከላይ በጽሁፉ አቅራቢ እንደተጠቀሰው፤ በእሰጥ አገባ ጉዳይ ጊዜን ለማጥፋት አቅሙም፣ ችሎታውም የለንም። አንድ ነገር ግን እንዲዘገብ እንፈልጋለን። መልስ የሚሹ የመወያያ እርእሶች ሲነሱ፣ በውይይት ለመፍታት የማነኛውም ብሎግ አላማ ይመስለናል። ከመወያየት የየግል ድክመቶችን ልንማር፣ ብሎም ልናርም እንችላለን። በዚህ ጽሁፍ የተጠቀሱት ሁሉ ከሌላው የተወረወሩትን ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ስለአመንበት ነው። የሌሎች ወንድምና እህቶችን መንፈስ ግን ለመጉዳት አሁንም፣ ወደፊትም አላማ የለንም። ማዋረድን፣ ስድብን፣ ጥላቻን ለማራገብ አላማችን አይደለም። እውነት የምንለውን ስንወረውር መዶዳዳት የለብንም። በአካል ልንከራከርበት የምንችለውን ያክል፤ በጽሁፍ መመካከር እንችላለን። አንድ ነገር ግን በድጋሜ መታወቅ ይኖርበታል። ውይይት አንድ ወጥ አለመሆኑን ማለት ነው። በዚህ ጽሁፍ ሐይለቃልና ከእውነት የተሰወረ ቀርቦ ከሆነ ልንታረም ዝግጁ ነን። የሌሎችን ወገኖች መንፈስ ያለአግባብ ሰብሮ ከሆነ ቢጠቆመን ይታረማል። በድጋሚ በቤተክርስቲያን ልይ ብቻ አተኩረን መወያየት የዚህ ብሎግ አላማ አይደለም። ትልቁ የአገርና የወገን ችግር አለና። ይህ የኛ አስተሳሰብ ነው። ሌሎች ደግሞ እንደቤት ስራ የከባቢን ጠበብ ብለውም ያንድ እምነትን ጉዳይ ብቻ ይዘው ሊቀጥሉ ይችላሉ። ለአስተያየትወ በጣም እናመሰግናለን። ሆደባሻ አለመሆን ነው። በቅን ልቦና ከተነጋገርን ችግርን ለመፍታት እንችላለን። ወንድማማቾች መሆናችን ግን አይረሳ።

    ReplyDelete