Wednesday, February 16, 2011

“Every generation needs a new revolution.”, Thomas Jeffersen

አብዮትን መድገም ይቻላል
ከሳᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

እንደሚታወቀው በአገራችን የቆየውን ባላባታዊ ስርአት ፈንቅሎ የጣለው የየካቲት አብዮት ዛሬ በሰሜን አፍሪካና በመላው የአረቡ አለም በመንጎድ ላይ  ካለው ሕዝባዊ አብዮት የሚመሳሰል ነበር። የካቲት ከመባቱ በፊት አያሌ የለውጥ ፈላጊ ትውልድ ትግሎች ተካሄደዋል። ዛሬ በግብጽ ያየነው አብዮት ላለፉት 18 ቀናት የተወለደ እንዳልሆነ ሁሉ። ከባእዳን እና ከአገር በቀል አሻንጉሊቶች ነጥቀው የግብጻውያን ለማድረግ ከአነዋር ሳዳትና ከጀማር አብደር ናስር ጀምረው ታግለዋል። የተለያየ ስምና መልክ እየተሰጣቸው ታሪካቸውና ስራቸው እየተወገዘ የወደቁበት ሳይታወቅ ያለፉ ታጋዮች ስማቸው ያልታወቁና በየፊናው በጓዳ ጎድጓዳው ወይንም በእየማፈኛ ጣቢያው ወድቀው ቀርተዋል። የባእዳን ተቀጣሪ አሻንጉሊቶች የነዚያን ታጋዮች ህይወት ከምንም ባለመቆጠር እስከዚህ የመጨረሻ ቀን ደርሰዋል። ባገራችን የካቲት ከመጠጋቱ ሰላሳና ሀያ አመታት በፊት በተለያየ መልኩ የታገሉት ባልባሌ ቀበሌወች በግዞት ታግተው ያለፉት የኢትዮጵያ ብርቅ ድንቅ ልጆች ብዙ ነበሩ። የበላይ ዘለቀና የሁለት አርበኛ ወንድማማቾች ሕልፈትና፤ ከነሱ ስቅላትና ሞት በኋላ በየቦታው ወድቀው የቀሩት ሁሉ የየካቲቱ አብዮት እርሾወች ነበሩ። የአፈንጉስ ደጃች ታከለ ወልደሐዋርያት ትግልና ሕልፈት የዚያ የየካቲቱ ሕዝባዊ ማእበል ቦይ ቆፋሪ ነበር። አብዮቱ ከመባቱ 13 አመታት በፊት በክቡር ዘበኛ መሪ ጀኔራል መንግስቱ ነዋይ፤ ገርማሜ ነዋይ፣ ጀኔራል ጽጌ ዲቡና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ እንዲሁም አያሌ ለውጥ ፈላጊ መኮንኖችና ተራ ወታደሮች ያለፉበት ትግል የዚያ የየካቲት አብዮታዊ ማእበል መንገድ ከፋች ነበር። ተከትሎም ለየካቲቱ አብዮት ሞተርና ሾፌር ሆነው ከዳር ያደረሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና መላ የተማሪውና የመምህራኑ ተስትፎ ለዚያ የአዲስ ምእራፍ ጎህ ቀዳጅ አብዮት አብዮተኛና የአብዮቱ ባለቤቶች ነበሩ። በጥቅሉ የየካቲት አብዮት ቀን ቆጥሮ የደረሰ ባይሆንም ከጣሊያን ወረራ ማግስት ጀምሮ የተደራረበ የትግል ውጤት ነበር። የካቲት 66 ከመባቱ ቀደም ብሎ በታሕሳስ 12 ከአምስት አመታት በፊት በዘውዳዊው አገዛዝ የጸጥታ ክፍል የተገደለውን ጥላሁን ግዛውን የሙት አመት ለማክበር እስከ ታሕሳስ 66 የሙት አመት ዝክር ሰላማዊ ሰልፍ በኢትዮጵያ ተማሪወች ይደረግ ነበር። የተማሪው ንቅናቄ ከፍም ዝቅም ሲል ተንኳቶ ታሕሳስ 66 ከረገጠ በኋላ ግን የማይመለስ ማእበል በመሆንና ያነገባቸውን ጥያቄወች ከምር አጥብቆ በመንቀሳቀሱ በአገሪቱ ከተከሰተው የወሎ እልቂትና አለማቀፍ የነዳጅ ዘይት ግሽበት ጋር በመጨመሩ። የአርበኛ ተመሪወችን ትግል ከታክሲ ሾፌሮች ጋር መደባለቁ፣ ብሎም የኢትዮጵያ ሰራተኛ በትግሉ ሙሉ ተፈጁን መሳተፍ መጀመሩ የተሜ ትግል የማይቆረጠም አጥንት ሆኖ ባተ። sector review እና የመሬት ለአራሹን ትግል ያነገበው ተማሪ ሰፍቶና መጥቆ ሌላውን የህብረተሰብ ትግል ጨመረ። የከተማ ነዋሪ የመንግስት ሰራተኛም ሆነ በገጠር የሚኖረው አርሶ አደር አጋርነቱን ሰጥቶ የአብዮተኛውን ወጣት ጉልበት አፈረጠመው።   በአንዳን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪወችና ዩኒቨርስቲው ትምሕርት ለቀው በመውጣት የተለመደውን የሰላማዊ ስልፍ ተይንት አድርገው ነበር። 1966 ታሕሳስ በግርግር ካለፈና ወጣ ገባ የሚሉ የተማሪወች ሰልፎች ከከተማ ከተማ መስፋፋት ጀምረው በጥር 4 ቀን የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮች እንዲሁም መምህራንና ተማሪወች የወሎ እርሀብን አስመልክቶ ሰላማዊ ሰልፎች አደረጉ። በዚሁ በጥር 4 በነገሌ ቦረና የአራተኛ ብርጌድ የሰራዊቱ አዛዦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ያስታወቀበትና ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ ወደትግሉ የተቀላቀለበት ጊዜ ታየ። ሆኖም ከጥር 4 እስከ በኋላ ለቀጠሉት ሰላሳ ቀናት የደመወዝ ጭማሪ ያደናገረው ወታደር ምንም ሳይል ይቆያል። ድሮውንም ለየካቲት አብዮት መወለድ ምክንያት የሆኑት ተማሪው አስተማሪውና ሰራተኛው እንዲሁም የባሌ አርሶ አደሮች አመጽና ለሁለት አመታት ከንጉሰ ነገስቱ ሰራዊት ጋር የጎበዝ አለቃውን መርጦ የተዋጋው የጎጃም አርⶃደር እንጅ፣ ወታደሩ የዚያን ስርአት አስጠባቂ ሆኖ የለውጥ ፈላጊ ታጋዩን የወገረና የገደለም ነበር።

ከጥር 4 እስከ የካቲት 11 ያለማቋረጥ ቦግ ድርግም ሲል በየፊናው የተማሪው ንቅናቄወች ቀጠሉ።፡የካቲት 5 የአየር ሐይል ሰራዊት የስራ ማቆም አድማ መታ። ተከትልሎ የካቲት 11 አንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር የስራ ማቆም አድማ አደረገ። ጥያቄወቹንም መልክ ባለው የስርአት ለውጥ አስፈላጊነትን አስታኮ አቀረበ። ከዚህ ጊዜ በኋላ እስከ የካቲት 21 ጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሐብተወልድ ስልጣን እስከለቀቁበት በሰሜን አፍሪካ ያየነውን ተመሳሳይ የሕዝባዊ ሰላማዊ እምቢተኝነት ትግሉ ተጦጧፈ። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በልጅ እንዳልካቸው ተተክተው መሾማቸውን ያስታወቁት ንጉሰነገስት። ሕዝቡ እልል ብሎ ሳይሆን ጉልቻ ቢለወጥ ወጥ አያጣፍጥም በሚል ትግሉን አስቀጠለው።

የካቲት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ጫፍ የደረሰበት ብሎም ስር ነቀል የስርአት ለውጥ የተደረገበት እንጅ ትግሎ ተጀምሮ ያለቀበት አልነበረም። ያትግል ምንም እንኳን ባላባታዊውን ስርአት ቢቀይርም ጥያቄወቹ እስከ ዛሬም ሳይመለሱ የቀጠሉበት፤ ብሎም የሕዝብ ምኞት በፋሽስት ጽልመት የደበዘዘበት ሌላ ምእራፍ ከፋች ወቅት ነበር።

የየካቲት አብዮት ያስገኛቸውን ድሎች በመንጠቅ እራሱን አቢዮታዊ ነኝ ብሎ የሾመው ወታደራዊ መንግስት ለትውልድ ጠባሳ ጥለው ያለፉ፤ በአገራችን ታሪክ ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ አሰቃቂ ወንጀሎች በመፈጸሙ፤ አብዮቱ ግቡን ሳይመታ ለመቀጨት በቅቷል።

የካቲትን መድገም ይቻላል

ላለፉት 35 አመታት የተካሄዱት ትግሎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። ሕዝብ ነጻነት ይፈልጋል። በመሆኑም ያነን የሕዝብ ፍላጎት ለማገድ ደርግም ሆነ ወያኔ/ኢሕአዴግ መልካም ሳይሆን አፈናን፣ እመቃንና ግድያን በመሳሪያነት ተጠቅመዋል። የነዚህ አንባገነን መንግስታት ማነኛውም አይነት በስልጣን ለመቆየት የሚያደርጉት ጸረ ሕዝብ ተጋድሎ ለጊዜው የተነሱ እንቢተኝነቶችን ሊያቀዘቅዝ ችሏል። የግብጽ አብዮታውያን ብዙወቹ በስርአቱ ዘመን ተወልደው ያደጉ እንደሆኑና ቀደምት ተጋድሎወች መክሸፋቸውን ከታሪክ ማሕደሮቻቸው ተምረው ወደትግሉ የገቡ በመሆኑ። ዛሬም የምእራብ አሻንጉሊት የሆነው ሙባረክ መውረድ አልፋና ኦሜጋ ነው። ትግሉን ጨረስን አላሉም። ዛሬ በግብጽ እንዴውም ካለፉት ትግሎች በሚያስቸግር እራስነ የማደራጀትና እርስ በእርስ የመስማማት መፍትሔ የሚሻ አስቸጋሪ አዲስ ምእራፍ እንደጀመሩ ተረድቷቸዋል።

ወደአገራችን ስንመለስ። የካቲትን መድገም እንደሚቻል አያሌ የሕዝብ ተጋድሎወችና በአመራር ጉድለት የከሸፉ አመጾች አስተማሪወች ናቸው።፡ዛሬ በአንዳንድ ተስፋ ቆራጮችም ሆነ የዚህ ስርአትን መቀጠል በሚፈልጉ ወገኖች የሚነገረው ኢትዮጵያ ውስጥ የሰሜን አፍሪካን አይነት አብዮት ማካሄድ አይቻልም የሚለው አስተሳስብ፡ ከፍ ሲል የጠላት ዝቅ ሲል አሞት የከዳቸው ወገኖች እንጅ፤ ዛሬም አብዮታዊ ሁኔታወችን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ብሶቶች ሞልተው ተርፈዋል።

ምርጫ 1997 እንዳሳየን ትግሉ ከምንጊዜውም በላይ በጎመራበት ሕዝቡ እንደክረም ጎርፍ በፈሰሰበት መሪና አስተባባሪ አግኝቶ ቢሆን ወያኔ የተባለ መናጢ የአናሳ ቡድንን ጠራርጎ ባባረረ ነበር። የዚያ ትግል መክሸፍ ዋነኛ ተጠያቂ በተቃዋሚነት ተቀምተው እንመራለን ያሉት እንጅ ወያኔ ሐይል ኖሮት እንዳልነበር ግልጽ ነው።

ሕዝብ ሲነሳ ሊያቆመው የሚችል አንድም ሐይ የለም። ይህንን የሕዝብ ሐያልነትን ዛሬ በሰሜን አፍሪካ በድጋሚ ብናይም ለእኛ የካቲት 66 ሕዝባዊ አብዮት ያለፍንበት የታሪክ ምስክር ነው።

አብዮት ይቻላል። ሕዝብ መነሳት አለበት

አንዳንድ ሰወች አገራችን በዘር ተከፋፍላለች ይሉናል። ይህንም እንደ አንድ ምክንያት በመውሰድ የግብጻውያንን አብዮት ማድረግ አይቻልም ለማለት ይጠቀሙበታል። ሌሎች ደግሞ የግብጽ ወታደሮች ስልጡን ስለሆኑ ሰው አልገደሉም ይሉናል። ይህም ወያኔ አይቻልም ለሚሉት ሌላው ሰበብ ፍለጋ መሆኑ ነው። እውነታው ግን ለየቅል መሆኑን በግብጽ የታየው አብዮት አሳየን። የገዥው የጸጥታና ፖሊስ ሐይል የቻለውን አደረገ፣ ገደለ በሰይፍም ሳይቀር አንገት ቀላ። በተሽከርካሪም በሰው ላይ ነዳ። ያም ቢሆን የበለጠ ሕዝብን ለቀጣይ ትግል አሰለፈው፣ እልህ ውስጥ አስገባው፣ የገዥውን ማንነትና ምንነት አሳየው እንጅ ወደቤቱ እንዲገባ አላረገውም። ያትግል ዛሬም ቀጥሏል። ምእራባውያንና የውጭ የጸጥታ ሀይላቸው ከአለማቀፍ ዲፕሎማሲ ጋር ሊያረጉት የሚችለው  አንድም ነገር እንዳሌለ በማየታቸው ሰልፋቸውን ቆርጦ ከተነሳው ጎን አሳመሩ።
የሙባረክ አልጋ በአመጽ ሲናወጥ፣ ዋሽንግተኖችና ለንደኖች ማረግ የሚችሉት ግራ ገባቸውና በየፊናቸው የተለያየ ሀሳብ መሰንዘር ጀመሩ። ከመሐላቸው መላ የሚፈጥር ግን አልተገኘም። ሙባረክ እህህ ብለው የወለዱት ልጅ ስለሆነ እሱን መክዳትና ጀርባ መስጠቱ እንደለመዱበት ከበዳቸው። የመጨረሻዋ ሰአት እናት ልጇን በላች እንዲሉ ካዱት። አናውቀውም፣ ክፉ አንባገነን ነበር አሉት።

መለስ ዜናዊና የወያኔ ቡችሎች እጣ ፈንታቸው ይህ እያየን ያለው አብዮት ነው። ኢትዮጵያውያን ዳግም አብዮት መስራት ይችላሉ። ሁኔታወችም ተመችተዋል። መቸውንም ቢሆን አንባ ገነን ገዥወች አብዮት ከቤታቸው በራፍ እስኪደርስ አይከሰትላቸውም። ትናንት በ ቀ.ሐ.ሥ አይተናል። የደርጉም መሪ እንዳንበሳ ባገሳበት፣ በገደለበትና በፈረደበት ከተማ ድምጹን ሳያሰማ እንደሾለከም ታዝበናል። ዛሬም በሰሜን አፍሪካ የአንባ ገነን ገዥወችን ባሕርይ ተመልክተናል። ሙባረክ ጠዋት ጓዙን ሊጠቀልል ማታ የሚያስፈራራ ግስላ በሚመስል አንደበቱ ወይ ፍንክች ብሎ ነበር። በጠዋት ግን የድመት ያክል ድምጹን አጥፍቶ ሸሸን ሰማን። የምእራብ አለቆቹም አብረው እንደሕዝብ ማውገዝና ማብጠልጠሉን ቀጥለዋል።

የመለስ ዜናዊና የተከታዮቹ እጣ ፈንታም ከዚህ የባሰ ነው። ዛሬ በዚህ ግቡ በዚያ ውጡ ብለው ያዘዟቸው የምእራብ አለቆቻቸው ያች ቀን ስትመጣ ውዳጁን ሙባረክን ካረጉት በከፋ ለነ መለስ ይጠብቃቸዋል። እንዴውም ተሎ እጅ ስጥ ሳይሆን፣ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ዶሴውን መምዘዝ ይጀምራሉ።

በኢትዮጵያ ዳግም አብዮት ማድረግ ይቻላል። የግድም እንዲሆን ያስገድዳል። ለዚያ ደግሞ ደፋር መሪወች እንፈልጋለን። ችግር ሲፈጠር የለንበትም የሚሉ አለያም ወደ አሜሪካን ኤንባሲ የሚሮጡትን አይደለም። ትግሉ ሲጠብቅ አብረው እንደልጥ፡የሚከሩ እንፈልጋለን። በወሬና የአሉባልታ ዘመቻ በሚያደነቁሩን መሪወች አገር ነጻ ልትሆን፣ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ግቡን ሊመታ አይቻለውም። ከቤት ሳይወጡ እናዋጋለን የሚሉ መሪወችን ማመን የለብንም። የነሱ ተስፋ ምእራቡ ነውና። ከመሬት ሳይነሱ ትልቅ ነን ብለው የሚንጠራሩ መሪወችም እንዲሁ አንፈልግም። ሞትን ሞተው ለማሳየት የሚሽቀዳደሙ መሪወች እንፈልግ። ሁሉም ባትሪ ይያዝ መሪን አገር ትወልዳለች፣ ሕዝብ መርቆ ይቀበላል።

ኢትዮጵያውያን አቢዮታችን በፋሽስቶች ከሸፈ ዳግም በጠባቦች ተደግማ በጨቋኞች እብሪት መሳቂያ መሳለቂያ ሆነናል። ከዚህ በኋላ በቃ ልንል ይገባናል።፡እኛም እንደግብጻውያን አብዮት መስራት እንችላለን። በአንባ ገነን መገዛት ያክትም፣ በለፈስፋሳ መሪወች መመራት ይብቃ፣ ሞትን የሚፈሩ፣ ለምእራብ ገዥወች ለሚሰግዱ፣ ከቤት ሳይወጡ ጦርነትን ለሚሰሩ ደግመን ደጋግ፣መን በቃ ልንላቸው ይገባል።፡የምርጫ 97 ሕዝባዊ ሱናሜውን የወያኔው የደህንነት ሰራትኛ ልደቱ መራው። ቀሪውን ፈሪወች ተሰባስበው የለንበትም አሉ። ዛሬ ያን መድገም ይገባል። ያን ስንደግም ጀግና መሪን መከተል፣ ፈሪን ማስወገድ ለጠባብ ብሔርተኛ ግብአተ መሬት ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል። በውጭ ያለ ሁሉ ከወሬ በዘለለ መነሳሳት ለውስጡ የመንፈስ ጥንካሬ ይሰጠዋል።

ኢትዮጵያ ዳግም አብዮት ልንሰራ ይገባል። በላይ ዘለቀን፣ አበበ አረጋይን፣ ታከለ ወልደሐዋርያትን፣ ገረሱ ዱኪን ልንውልድ ግድ ይለናል። ተስፋየ ደበሳይን፣ ጸጋየ ገ/መድህንን፣ ጋይምን፣ ወንዱ ሲራክን፣ አይነት መሪወች ዛሬ ከመቸውም በላይ እንፈልጋለን። ጥሪው ይድረስ ለአብዮተኛ መሪወች፣ ለወጣትና ለአባት አርበኞች። አገር ዳግም አብዮት ልትሰራ ትጣራለች። ሁላችንም መነሳት ይገባናል። ፍጹም ነው እምነቴ፣ ለአብዮቱን ነው ሕይወቴ ብለን እንነሳ።

ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!