Monday, May 16, 2011

A society of sheep must in time beget a government of wolves. - Bertrand de Jouvenel

ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት [ዳኛቸው አሰፋ (ዶክተር)]

በሌላ በኩል ግድቡ የተሰጠው ስያሜ ሕዳሴ ነው። ሕዳሴ የሚለው ስያሜ አንድ የሚጠቁመን ነገር አለ። ስሙ ራሱ ከሂስ እና ከትችት ጋራ የተቆራኘ መኾኑን እንገነዘባለን። በመኾኑም የሕዳሴ ጀምሬያለሁ ግን ሂስ (Criticism) አይኖርም ማለት አይቻልም። ሕዳሴ እና ትችት እየተመጋገቡ የሚሄዱ ስለኾነ ዜጎች በፕሮጀክቱ ዙርያ ብዙ ጥያቄዎች የማንሳት መብት አላቸው። ራዕዩ በጎ ስለኾነ ምንም ዐይነት ጥያቄ ማንሳት አይቻልም የሚለው አቀራረብ ትክክል አይደለም። ስሙ በራሱ ትችትን ይጋብዛል። ከዜጎች ከሚጠበቀው መዋጮ ብቻ እንጂ ግድቡን በሚመለከት እኛ ካልነው ሐሳብ ውጭ አስተያየት ሊቀርብ አይችልም የሚለው አካሄድ ትክክል ኾኖ አናገኘውም።
ዳኛቸው አሰፋ (ዶክተር)
የጽሑፌ ዐብይ ጉዳይ የተመሠረተው ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አድማሱ ጸጋዬ ባቀረብኩት ግልጽ ደብዳቤ ላይ ነው። ከዚያ በፊት ግን ለመንደርደርያ የሚኾን አንድ ሁለት ነገሮችን ስለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ስለ ዐባይ ሕዳሴ ፕሮጀክት ጥቂት ብለን እናልፋለን። ከበርካታ ተግባሮቹ መካከል አንድ ዩኒቨርሲቲ በተቀዳሚነት ከሁለት በኩል የሚመጡ አመለካከት እና የአስተያየት ግፊቶችን የሚቋቋም ደጀን ነው። በመኾኑም ከሁለት በኩል ማለትም በአንድ በኩል ከፐብሊክ ኦፒኒየን (Public opinion) በሌላ በኩል ከኦፊሻል ኦፒኒየን (Official opinion) ሐሳቦች የሚመረመሩበት እና የሚፈተሽበት ቦታ ነው።
ፐብሊክ ኦፒኒየን የራሱ ሐሳቦች አሉት። ኦፊሻል ኦፒኒየን ደግሞ በመንግሥት ዙርያ የሚያጠነጥኑ ሐሳቦችን ይይዛል። እነኚህ ሁለት ሐሳቦች ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚመጡበት ጊዜ እንዳለ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አያገኙም። አንድ ዩኒቨርሲቲ እነዚህ ከሁለት ወገን የሚመጡ ሐሳቦች የሚፈተሹበት መዲና ነው። ስለዚህ ይህንም ለማድረግ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ ፍጹማዊ የኾነ ሉዓላዊነት እና ልዕልና እንዲኖረው ይገባል። በአጠቃላይ የየትኛውም የዩኒቨርሲቲ ታሪክ እንደሚያስተምረን በተለያየ ጊዜ እና በተለያየ መልክ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ አሉታዊ ግፊት ከውጭ (ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት፣ ከባህላዊ፣ ከማህበራዊ ወዘተ . .) ሊንጸባረቅ ይችላል። የአሜሪካ እና የአውሮፓ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ባለንበት ዘመን እነርሱ ላይ የሚደርሰው ግፊት ከኮርፖሬት ካፒታል(Corporate capital) ፍላጎት ጋራ በተያያዘ መልክ የሚደርስ ነው።
አዲሱ የካፒታሊዝም አደረጃጀት የኾነው ኮርፖሬት ካፒታል ዩኒቨርሲቲዎቹ እርሱ የሚፈልጋቸውን ጥናቶች እንዲያካሂዱ ጫና ያሳድራል። የራሳቸው የኾነ ተልዕኮ እንዲኖራቸው አይፈልግም። እንዲሁም ተማሪዎችን ካምፓኒዎቹ በሚፈልጉት ልክ እያሠለጠኑ እንዲያወጡ ተጽዕኖ ያደርጋል። ወደ እኛ አገር መለስ ስንል መንግሥት የ“ልማት” እና የ“ግንባታ” ጥሪ ይዞ ስለቀረበ ይኼን ተልዕኮ ዩኒቨርሲቲው በተቀዳሚነት አጋር ኾኖ የልማት አጀንዳ አስፈጻሚ መኾን ይጠበቅበታል ብሎ ያምናል። ስለኾነም ይህን ተልዕኮ ለመፈጸም ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አደረጃጀት እና አወቃቀር ላይ የተመረኮዘ ራዕይ ይዞ የልማት አጋር መኾን አለበት ብሎ ስለሚያምን በዩኒቨርሲቲው አደረጃጀት እና ራዕይ ላይ ጫና ይፈጥራል። ኾኖም ግን አንድ ዩኒቨርሲቲ ከተነሳበት የጥናት፣ የምርምር እና በአጠቃላይ እውቀትን የማዳበር ተልዕኮ ወጥቶ በግፊት በዋነኝነት ለሌላ ጉዳይ አገልጋይ ከኾነ ዩኒቨርሲቲው እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሊያበረክት አይችልም። ዩኒቨርሲቲው “እንደ ዩኒቨርሲቲ” እንዲቀጥል ከተፈለገ ከራሱ ተልዕኮ እና ግብ ውጭ የሚመጣውን ግፊት ተቋቁሞ ሉዓለዊነቱን ማስከበር አለበት።
በሁለተኛ ደረጃ ወደ የዐባይ ፕሮጀክት ስንሄድ . . . ይኼ ፕሮጀክት ከሁሉም በላይ ለየት ያለ በጎ ነገር ይዞ መጥቷል ብዬ አምናለሁ። ለኻያ ዓመታት የብሔር፣ የጎሳ፣ የክልላዊ ፖለቲክስ የበላይነት በያዘበት ኹኔታ ላይ ፕሮጀክቱን ይህን ዐይነት አመለካከት እና የፖለቲካ አካሄድ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ እና የሻረ ኾኖ እናገኘዋለን። ስለኾነም ዐባይ ክልላዊ ማዕቀፍ የሌለው፣ የትኛውም ክልል ላይ ያለ እና የየትኛውም ብሔር አባል ኢትዮጵያዊ “የእኔ ወንዝ ነው” ሊለው የሚችል በመኾኑ ሁላችንንም የአንድ አገር ልጅ ወይም የአንድ ወንዝ ልጅ መኾናችንን የሚያበስር ነው። ግድቡን ከዚህ አኳያ ስናየው ክልላዊነትን፣ ጎሳዊነትን፣ ነገዳዊነትን ተሻግሮ ከባንዲራ ቀን ቀጥሎ ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ብሒል ያበሰረ እና የተዳፈነውን ብሔራዊ ስሜት እንደገና እንዲያቆጠቁት ያደረገ ነው።
በሌላ በኩል ግድቡ የተሰጠው ስያሜ ሕዳሴ ነው። ሕዳሴ የሚለው ስያሜ አንድ የሚጠቁመን ነገር አለ። ስሙ ራሱ ከሂስ እና ከትችት ጋራ የተቆራኘ መኾኑን እንገነዘባለን። በመኾኑም የሕዳሴ ጀምሬያለሁ ግን ሂስ (Criticism) አይኖርም ማለት አይቻልም። ሕዳሴ እና ትችት እየተመጋገቡ የሚሄዱ ስለኾነ ዜጎች በፕሮጀክቱ ዙርያ ብዙ ጥያቄዎች የማንሳት መብት አላቸው። ራዕዩ በጎ ስለኾነ ምንም ዐይነት ጥያቄ ማንሳት አይቻልም የሚለው አቀራረብ ትክክል አይደለም። ስሙ በራሱ ትችትን ይጋብዛል። ከዜጎች ከሚጠበቀው መዋጮ ብቻ እንጂ ግድቡን በሚመለከት እኛ ካልነው ሐሳብ ውጭ አስተያየት ሊቀርብ አይችልም የሚለው አካሄድ ትክክል ኾኖ አናገኘውም። ለመግቢያ ይህን ካልኩ ወደ ደብዳቤዬ ላምራ።

ይድረስ ለክቡር ፕሬዝዳንት፤
ዶክተር አድማሱ ጸጋዬ
ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ግልጽ ደብዳቤ የምጽፍልዎ በቅርቡ ያለፈው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ላይ እንደተደረገው ድረ-ገጽን ወይም ጨለማን ተገን አድርጌ በድብቅ ስለ እርስዎም ኾነ ስለ ዩኒቨርሲቲው መበተን ስላልፈለግኹ ነው። ይህም እምነቴ የመነጨው የዩኒቨርሲቲው መምህራን በተለያየ ጉዳይ እና ርእስ ፊት ለፊት ወይም ስማቸውን ገልጸው የመናገር መብት ብቻ ሳይኾን የሞራል ሐላፊነትም አለባቸው ብዬ ስለማምን ነው።
በሌላ በኩል ይህን ደብዳቤ በምጽፍበት ወቅት ሁለት ነገሮች አሳስበውኛል። አንደኛ እርስዎ ገና እዚህ ዩኒቨርሲቲ መምጣትዎ ነው። እናም ከመምጣትዎ እና ሥራ ከመጀመርዎ እርስዎን ወደ ትችት ይዞ መሄድ ትክክል መስሎ ስላልታየኝ፤ ሁለተኛ እኔም ብኾን ገና ሦስተኛ ዓመቴን ጨርሼ ወደ አራተኛ ዓመት እየሄድኩ ስለኾነ ዩኒቨርሲቲውን በሚመለከት አጠቃላይ ሂስ እና ክርክር ውስጥ ለመግባት እንደው “ፍየል ከመድረሷ . . “ እንዳያሰኘኝ ፈራ ተባ እያልኹ፤ ኾኖም ግን መባል ያለበት ነገር መባል አለበት ብዬ ስለማምን እና በሁለተኛ  ደረጃ ደግሞ “በመጀመርያ ላይ ያለች ትንሽ ስህተት በሁዋላ ትልቅ ትኾናለች” የሚል ትምህርት እና እምነት ስላለኝ ውይይቱ እና ግልጽ ንግግሩ ተገቢ ነው ከሚል ነው የተነሳሁት።
ለደብዳቤዬ የፍልስፍና መነሻ እና መሠረት የኾኑኝ የታላቁ የጀርመን ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት አስተምህሮት እና በቅርቡ ታሪካችን ለነጻነት የተደረገው ትግል ነው። በአንድ ወቅት ስለ “ብርሃነ-ሕሊና” ወይም “አብርሆት” ስለሚባለው ዘመን ካንት ሲያስተምር ስለዜጎች መብት የሚከተለውን ብሎ ነበር። “አንድ ግለሰብ የሁለት ዐይነት ምክንያታዊነት ባለቤት ነው። አንደኛውን ‘ግለሰባዊ ምክንያታዊነት’ (Private use of reason) ሲኾን ሁለተኛው ‘ማሕበረሰባዊ ምክንያታዊነት’(Public use of reason) ነው። ማንኛውም ሰው በተመደበበት የሥራ ዘርፍ ውስጥ ‘ግለሰባዊ ምክንያታዊነቱን’ ተጠቅሞ ሥራውን ያለምንም ማቅማማት ማከናወን አለበት። ከተመደበበት ሥራ ውጭ ደግሞ ‘ማሕበረሰባዊ ምክንያታዊነቱን’ ተጠቅሞ ስለ ሥራውም ኾነ ስለሌላ ጉዳይ የመተቸት እና የመሄስ መብት አለው። ይኼን ለማድረግ ደግሞ የነጻነት መኖር ወሳኝ የኾነ ቅድመ ኹኔታ ነው” ይላል። ነጻነት ከሌለ ‘ማሕበረሰባዊ ምክንያታዊነት’ን መጠቀም አንችልም ነው የሚለው። እንደውም ይኼ ነጥብ አምባገነናዊ ሥርዐትን እና ዲሞክራሲያዊ የኾነውን ልንለይበት የሚያስችል ሐሳብ ነው። አምባገነን አገዛዝ ‘ግለሰባዊ ምክንያታዊነትን’ ይፈቅዳል። በሥራ ዘርፍ የፈለከውን ዐይነት ‘ግላዊ ምክንያታዊነት’ የመጠቀም መብት አለህ። ችግር የሚመጣው ግን ከፍ ብለህ ‘ማሕበረሰባዊ ምክንያታዊነትን” ለመጠቀም ስትከጅል ነው። መተቸት አትችልም፣ ቅሬታ ማሰማት አትችልም፣ ሌላ ሐሳብ ማቅረብ አትችልም ትባላለህ።
እኔም እንደማንኛውም ዬዩኒቨርሲቲ መምህር ግለሰባዊ ምክንያታዊነቴን በመጠቀም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለቆቼ የሚያዙኝን በተሰጠኝ የሥራ ድርሻ የሐላፊነቴን እየተወጣሁ ነው። በተረፈ ግን ማሕበረሰባዊ ምክንያታዊነቴን በመጠቀም ስለ ዩኒቨርሲቲውም ኾነ ስለማንኛውም ጉዳይ እንደ ዜጋ የመናገር እና የመተቸት መብት አለን ብለው ከሚያምኑት ወገን ራሴን አሰልፈዋለሁ።
‘ማሕበረሰባዊ ምክንያታዊነትን’ ለመጠቀም ነጻነት ወሳኝ ነው። የአገራችን የቅርብ ታሪክ እንደሚያሳየው ለነጻነት ብዙ ዋጋ እና መሥዋዕትነት ተከፍሏል። እኔም ኾንኩ እርስዎ እንደሚያውቁት ከአሲምባ እስከ ደደቢት በረሃ ድረስ የብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሕይወት የተከፈለበት ነው። በመኾኑም እኔ ይህ ሕይወት ዋጋ የተከፈለበት የዲሞክራሲ ተስፋ ጭላንጭል እንዳይዳፈን እሳቱ እፍ እፍ መባል አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህን አለማድረግ ግን እሳቱን ላቀጣጠሉት እና ለተሰዉት ክብር አለመስጠት ነው።
ክቡር ፕሬዝዳንት የዐባይን የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ የዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ ምን ማድረግ ይገባዋል? የሚለውን ለመመለስ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ባቀረበው ጥሪ መሠረት ሚያዝያ 21 ቀን 2003 ዓ.ም እርስዎ በመሩት ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር። የቀድሞው የኢሠፓ ዋና ጽ/ቤት የነበረው አዳራሽ ውስጥ በነበረን ስብሰባ ወቅት ያሳሰቡኝን ሁለት ነገሮች በተመለከተ ለእርስዎ ጥያቄዎች ለማንሳት ተገድጄያለሁ። አንደኛው ንግግርዎን ከቋጩ በሁዋላ ተሰብሳቢዎች ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ጋበዙ። እኔ እስከማስታውሰው ድረስ አምስት ይኹኑ ስድስት ሰዎች ተነስተው ተናግረዋል። እነኚህ ሰዎች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሥራ ዘርፎች የመጡ ናቸው። ሁሉም የተናገሩት “እኔ” እያሉ ነው። በግላቸው “የአንድ ወር ደመወዛችንን እንሰጣለን”፣ አንዳንዱ ደግሞ “ተጨማሪም መስጠት እንችላለን”፣ ሌሎቹ “የሚመጣው ዓመት እንዲቆረጥብን . .” ብቻ በተለያየ መልኩ “እኔ እንዲህ አደርጋለሁ”፣ “እኔ እንደዚህ ለማድረግ አስባለሁ” ነው ያሉት። አሁን እኔን የቸገረኝ ነገር እነኚህ ሰዎች የተናገሩት ለራሳቸው ኾኖ ሳለ እንዴት አድርገው ነው እርስዎ ውይይቱን ሲቋጩ “ . . . እንግዲህ እየተደጋገመ የመጣው ሐሳብ ተመሳሳይ ስለኾነ ወደ አጠቃላይ ውሳኔ እንግባ” ያሉት? “አጠቃላይ ውሳኔው የአንድ ወር ደሞዛችንን መስጠት አለብን ነው የሚለው” ብለው ደመደሙ። እኔን የገረመኝ አምስት እና ስድስት ሰዎች ስለራሳቸው ካደረጉት ንግግር ተነስተው እንዴት አድርገው ነው “አጠቃላይ ውሳኔን” ወይም የዣን ዣክ ሩሶን “General Will” እንዳገኙት ነው።
ሩሶ “አንድ ሐሳብ በፓርላማ ውስጥ ሲቀርብ እያንዳንዱ የፓርላማ አባል እና ሕግ አውጭው ተቀባይነት ያገኘው የእኔ ሐሳብም ነው ብሎ ሲያምን ማለትም የግለሰቡ ሐሳብ እና የቤቱ ሐሳብ አንድነት ሲያገኝ General Willን (አጠቃላይ ፈቃድን) ያንጸባርቃል” ይላል። ይህ ጽንሠ ሐሳብ በሁዋላ ላይ አክራሪነት ስለኾነበት ሩሶ Will of all (የብዙሃኑ ሐሳብ) ብሎ አሻሽሎታል። Will of all (አጠቃላዩ ሐሳብ) የሚገኘው በድምጽ ቆጠራ ነው። እዚያ አዳራሽ ውስጥ እኔ እስከሚገባኝ እንኳን “General Will” (አጠቃላይ ፈቃድ)፣ Will of all (የብዙሃን ፈቃድ) የተገኘ አይመስለኝም። ተገኘ የተባለው “Will of all” ቢያንስ ድምፅ በመስጠት እያንዳንዱ ድምፅ ተቆጥሮ- እያንዳንዳችን እጃችንን አውጥተን ይኼን ያህል ፐርሰንት እንደዚህ ያስባል ተብሎ ቁርጥ ያለ ወደ “አጠቃላይ ውሳኔ” የሚወስድ አሃዝ እና የሐሳብ አዝማሚያ አልታየበትም። ትክክለኛ መንገድ ሳይያዝ እንዲሁ በአጠቃላይ “የአጠቃላይ ውሳኔ” ላይ ደርሰናል ተባለ። ይህ ብዙ ጥያቄዎች ሊያስነሳ ይችላል።
አንደኛ፦ ክቡር ፕሬዝዳንት እንደሚያውቁት በ“ግዳጅ” እና በ“ፈቃድ” መካከል ልዩነት አለ። በፈቃድ ከኾነ አንድ ሰው እኔ አላዋጣም የማለት መብት አለው ማለት ነው። ወይም ደግሞ ሌላ አማራጭ መንገድ ነው ይዤ የምሄደው ለማለት ይችላል ማለት ነው። የእኔ ጥያቄ እዚያ የተሰበሰብነው ሰዎች የወር ደሞዛችንን እንደንሰጥ የተደረግነው ባለፈው ሥርዐት እንደተደረገው በፈቃድ ሳይኾን በግዳጅ ነው? የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የወር ደመወዝ ለመውሰድ ሕጋዊ መሠረትስ አለው ወይ? በግዳጅ ከኾነ ምንም የሚያጨቃጭቅ ነገር የለም። አንድ ሰው ተገዶ ማድረግ ያለበትን ያደርጋል። አሁን እየተባልን ያለው ግን “በፈቃድ ነው” ነው።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ እና የኦፊሻል ሐሳቦች የሚፈተሹበት ስፍራ ነው እንዳልነው፤ በሁለቱ ጎራዎች ተቀባይነት እና የበላይነትን የያዘው ሐሳብ “ማንኛውም ሠራተኛ፡_ የወር ደመወዙን ይስጥ” በሚለው መርህ ዙርያ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል ብዬ አስባለሁ። አንዲት 400 ብር የሚከፈላት የሁለት ልጆች እናት የኾነች የፅዳት ሠራተኛ እና አንድ የብዙ ሺሕ ብሮች ገቢ ያለው አስተማሪ ወይም ሐላፊ እንዴት እኩል የወር ደሞዛችሁን ስጡ ይባላሉ?
ሁለተኛ፦ በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ “ . . ከመውጣታችሁ በፊት ትንሽ ቆዩ” ተባልንና የአቋም መግለጫ ተብሎ አምስት ነጥብ ይመስለኛል  . . . እዚያ ያልጻፍነው ከውጭ ተጽፎ የመጣ ልክ እኛ እንዳረቀቅነው ተደርጎ ተነበበ። ሲጀመር የአቋም መግለጫ ማለት ምን ማለት ነው? ይኼ እኮ የፖለቲካ ፓርቲ ስብሰባ አይደለም። ሁላችንም ግለሰቦች እና መምህራን ነን። በአንድ ፓርቲ ስር የተሰባሰብን አባላት አይደለንም። የእኛ የአቋም መግለጫ ሲባል ምን ማለት ነው? ከአሁን ጀምሮ ግድቡ ተሠርቶ እስከሚያልቅ ድረስ አቋማችን ይኼ ነው ማለት ነው?
ከሁሉም ደግሞ ከአቋም መግለጫው አንደኛው ላይ የሚገርም አነጋገር ነው ቀረበው። “ . . . ይኼን ነገር የሚጠይቅ እና አንዳንድ ነገሮችን  . . . ሥነ ልቡናዊ ጫና የሚያመጣውን ሁሉ እንታገላለን” ይላል። ይኼ በእውነት የካድሬ ስብሰባ የሚያስታውስ ነው እንጂ ለአንድ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጥ ክብርን ያላካተተ አካሄድ ኾኖ አግኝቼዋለሁ።
የ19ኛው ክፍለዘመን ትልቁ ፈላስፋ ጆን ስቱዋርት ሚል(Liberty) ነጻነት በሚለው ጽሑፉ አንድ ቦታ ላይ፤ “የሕዝብ ፕሮጀክት እና የመንግሥት ፕሮጀክት አንድ የኾነ ዕለት፣ ስምምነት ላይ የደረሰ ዕለት የግለሰብን መብት ለመርገጥ በጣም አመቺ ኹኔታ ይፈጠራል” ይላል።  በእኛ አገር አነጋገር መብት ለመርገጥ “ሰኔ እና ሰኞ ገጠመ” ማለት ነው። ሚል ኹኔታውን ሲያብራራው  “. . . ይህን ወቅት በጣም ነው የምፈራው። ያኔ የግለሰብን መብት ለመርገጥ አመቺ ኹኔታ ይኖራል” ነው የሚለው። እኔም እንደዚህ ዐይነት ነገር ነው እዚያ አዳራሽ ውስጥ ያየኹት። የዐባይ ግድብ ጉዳይ የተወደደ እና ድጋፍ ያለው ሐሳብ ስለኾነ ብዙ መምህራን ደፍረው እንኳን ለመጠየቅ አልቻሉም። በሌላ በኩል የስብሰባው አካሄድ የውይይትን እና የምክክርን መንፈስ የተላበሰ አልነበረም።
ክቡር ፕሬዝዳንት አሁን በቅርቡ የያዙት ሐላፊነት የተሳካ እና የሥራ ጊዜ ኢንዲኾንልዎ በመመኘት ደብዳቤዬን እያጠቃለልኩ የቀረበውን ትችት በቀናነት ይመለከቱታል የሚል ተስፋ አለኝ።
(ዳኛቸው አሰፋ (ክተር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ዲፓርትመንት አባል እና የኢንስቲቲዩት ኦፍ ሂዩማንራይት ፌሎው ናቸው።)
ምንጭ- አዲስ ጉዳይ መጽሔት