Monday, March 28, 2011

The manufacturer who finds himself up the creek is the short-sighted opportunist who siphons off all his advertising dollars for short-term promotions.” David Ogilvy

የጣረሞቱ ሕወሐት/ኢሕአዴግ የሰሜን አሜሪካ የስብሰባ ዘመቻ

ትዝ ይላችሁ ይሆናል፤ 1991 ወያኔ የምእራቡና የጸረ ኢትዮጵያ አረብ አለም የጫጉላ ልጅ ሆኖ ምንም የሚያቆመው ወታደር በሌለበት በሱዳን የብረት ለበስ ካሚወኖችና በፔትሮ ዶላር ታግዞ ለሰላሳ አመታት የኢትዮጵያ አንድነትን ከተፈታተነው አገር ገኝጣዮች ጋር በመሆን አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት፣ ዘመቻ ዋለልኝ፣ ዘመቻ ቴወድሮስ ዘመቻ ምናምን እያለ የሰየመው የውጊያ ቀጠና ነበር። በሰሞኑ ያነን በሚያስታውስ የዘመቻውን ስም ባንሰማም በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ያውም ሰሚ ጀሮ በሌለበት እነዚያው ደናቁርት እበላ ባዮችን ለመሰብሰብ በአላሙዲን የገንዘብ ድጋፍ ዘመቻውን እንደሚጀምር ሰማን።

ነገሩ እንዲህ ይጀምራል ከዚህ በታች ያለውን ብትከፍቱት የአጀማመሩን አይነት ለማየት ይቻላል።

በጃንዋሪ መጨረሻ በሸራተን አዲስ አበባ ሆቴል ይህ ከላይ በዋልታ የተዘገበውን ስብሰባ አዲሱ የመለስ ቡድን ሹመኛ የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይጠራሉ። ከላይ በተለጠፈው ቪዲዮ እንደሚታየው በዛ ያሉ ወዳገራቸው ጎራ ብለው የነበሩ ውጭ ነዋሪ ኢትዮጵያውያንና ለዚሁ አሸባሪ ዘረኛ ቡድን ደጅ በመጥናት ላይ የነብሩ ግለሰቦችም ተጨምረው የተደረገ የፕሮፖጋንዳ ስራ ነበር። ሰባስበው የተለመደ የሕወሐት/ኢሕአዴግ የማያልቅ የፖለቲካ ቧልት ስለሆነ ባይገርመንም አንድ አምስት አመት ሄዶ ሌላ ሲተካ የአምስት አመት እቅድ ግቡን መታ የአምስት አመት እቅድ በዚህ ወጦ በዚህ ገባ ሲሉን ይኸው ድፍን ሀያ አመታት መሆኑ ነው። ያየነው እቅድ አገር ሲያስገነጥሉ ወይንም ያገር ሀብትና ንብረት ሲቸበችቡ ነው። ዛሬ ለምን ወደውጭ መውጣት እንዳስፈለጋቸው ባናውቅም፤ በነጻነት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እነሱን ጠልቶ አገሩን ትቶ የሚኖር በመሆኑ ምን እናገኛለን ብለው ይህን ዘመቻ ለመጀመር እንደዘየዱ ባይገባንም፤ከዚህ በፊት በየከተሞች ዞረው  ባደረጓቸው ስብሰባወች እንደአበደች ውሻ አንያችሁ ተብለው ሲረገሙ እንጅ ሲመረቁ አላየንም። የሚያስመርቅም የሰሩት ባለመኖሩ እነሱም ያውቁታልና ነው።

በመጀመሪያው የሸራተን ስብሰባ በፕሮፖጋንዳ መስሪያቸው ቪዲዮ እንዳየነውና፤ የሕወሐት የፕሮፖጋንዳ መሐከል የሆነውም እንደዘገበው ተወያየን ከማለት ውጭ የውይይት ውጤት ሲፈጸም ግን አላየነም። በዚያ ስብሰባ የተገኙ ከአንዱ ግለሰብ በስተቀር ሁሉም የዚህን አገዛዝ በዳይነትና ጎጅነት በትክክል ገልጸዋል። ታዲያ ዋልታ ይህችን አይነት ለነዋሪው ሕዝብ ያልፈቀዳትን እንወያይ ለፕሮፖጋንዳ ሲጠቀምባት ምን አስበው ማለት ይገባልና፤ በዚህ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ሊያደርጉ ያሰቡት ሁለት ነገር መሆኑን እንረዳለን። አንደኛው ደጅ ሊጠኑ የከጀሉትን ማሰባሰብ ሲሆን፣ ሌላው መንግስታችን ልዑካን አሰማርቶ ከዲያስፖራው ጋር ተወያየ የሚል ሌላ የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ማግኘት ነው። ከዋልታው ምስል እንዳየነው ከዚህ ከዳላስ የሄደ ጸሐይ ጽድቅ ቤተማርያም የተባለ ግለሰብ “ከዚህ የተሻለ መንግስ ከሰማይ እንደመና አይወርድም” አከታትሎም “ አትፍሯቸው መጣችሁ ሰብስቡን” እንዳለው፤ ሕወሐት/ኢሓዴግ ተመሳሳይ ሰወችን እየሰበሰበ ሕዝቡን ለማሳየትና አርፈህ ተቀመጥ ሰፊ ድጋፍ አለኝ ለማሰኘት የተዘየደ መሆኑ ነው። ነገርን ነገር ያነሳዋልና ከዚህ ከዳላስ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ በሸራተን ስብሰባ ተገኝቶ እንደተናገረው በእርግጥም ብዙ መልካም ነገር እየሰራላቸው እንደሆነ ዳላስ ነዋሪ የሆነው ዜጋ ሁሉ ያውቃል። ግለሰቡ በደርግ ተሿሚ የነበር። የአስመራ ከተማ የኢሰፓ ካድሬ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን አሁን ደግሞ እዚህ ዳላስ ቤተክርስቲያን ከሶ ሕዝብ ያሳዘነና ለሰራው መልካም ስራ በወያኔ ባሕርዳር መሬት ተሰጥቶት ሕንጻ ለመስራት ደፋ ቀና በማለት ላይ ያለ ነው። ለነገሩ እየወደቀ ባለ ዛፍ ለመንጠልጠል ምን እንዳስመኛቸው ባናውቅም አሁንም ሕወሐት/ኢሓዴግ ለእሚያደረገው የውጭ ስብሰባወች ደፋ ቀና ባዮች፣ የስብሰባ ቦታ አዘጋጆችና ከፊት አብሪወች ከሕወሐት የትውልድ ቦታ የተፈጠሩ ሳይሆን የዚህን ግለሰብ አይነት እናገኛለን ያባት ቤት ሲወረር አብረሕ ውረር በሚል ፈሊጥ የተነሳሱ ግለኞች ናቸው። አንዳንዶቹም መልካም ኑሮ ያላቸው ሆኖ ሳለ ለምን ወዶ ገብ ሊሆኑ እንዳሰቡ ባናውቅም፣ ውስጠ ባህርያቸው በሰው ተረማምዶ የኔ የሚሉት ሐብት ንብረት ማካበት ነው። እርሐብ፣ ስራ አጥነትና የጎዳና ተዳዳሪነት በከፋ መልኩ በተንሰራፋባት አገር ሕዝብን በጢሙ ደፍቶ አገርን እየቸበቸበ ካለ መንግስት ጋር መወገን ከወንጀለኛው  በላይ ወንጀል ፈጻሚነት ነው። http://www.guardian.co.uk/global-development/video/2011/mar/21/ethiopia-land-rush የአገር መሬት እንዴት እየተሸጠ እንዳለ ከዚህ ዋቢ ቪዲዮ ማየት ይቻላል። መክፈት ካልቻሉ press ctrl key and double click the link.  

የወያኔ የስብሰባ ጥሪ በዳላስ

በአፕሪል 9, 2011 ወያኔ ኢሓዴግ በደብዳቤ እያሾለከ የላከው የስብሰባ ጥሪ እንዳለ ሰምተናል። የኮሚውኒቲአችንን ሬዲዮ በመጠቀም ስብሰባውን ጠሪወችም ከላይ እንደጠቆምሁት የፀሐይ ጽድቅ ቤተማሪያምና እዚህ አገር ተምሮ መልካም ስራ ያለው አንድ ኤንጅነር እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። ይህ የስብሰባ ጥሪ በዳላስ ብቻ እንዳልሆነም ለማወቅ ችለናል።አንባገነኖችን እየጠራረገ ያለው የሰሜን አፍሪካ አብዮት አገራችን መግባቱ የማይቀር መሆኑን ከተበደለው በላይ በዳዩ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ የተቃውሞ ምንጭ ነው የሚለውን የዲአያስፖራ ዜጋ ለመከፋፈል ባሰማራቸው አዳዲስ ወዶገባወች እየተመራ ከፍተኛ ወጭ አውጥቶ የካድሬ ስራ ለመስራት የጠባቡ ቡድን  ታማኝ አባላቱን አሰማርቷል። በአንድ ቀን ብቻ ማለትም አፕሪል 9 ቀን 2011 በ14 የሰሜን አሜሪካ ከተሞች ስብሰባወች ተጠርተዋል። ቡድኑ ለስብሰባ የሚመጡት እነማን መሆናቸውን እያወቀ፣ ቢፈልግ ወደየ ኤንባሲ መስሪያ ቤቶች አስጠርቶ ማናገር ሲችል፤ ለፕሮፖጋንዳ እንዲሆነው፣ ብሎም በስደት የሚኖረውን ዜጋ ለመከፋፈል ሲል ከደሐ ሕዝባችን አፍ የነጠቀውን ላላስፈላጊ ተግባር በማን አለብኝነት እያዋለው ይገኛል። በዚህ ቀን ለሚደረግ ስብሰባ ሁሉም በውጭ የሚኖረውና በተለየም ስብሰባው በተጠራባቸው ከተሞች ነዋሪው ሁሉ ስብሰባው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መሆኑን ለወገን ማስገንዘብ ያስፈልጋል። ማንም ኢትዮጵያዊ ላገር ለወገን የሚቆረቆር ወደነዚህ ስብሰባወች እንዳይሄድ ጥሪ ሊደረግ ይገባል።

የስብሰባው አጀንዳና የዘመቻው ምክንያት

የነዚህ ስብሰባወች አጀንዳና የሕወሐት/ኢሕአዴግ የሰሜን አሜሪካ  ዘመቻ ምክንያት የመጭ አምስት አመታት እድገት በሚል የታጀለ ነው። በመሰረቱ የወያኔው መሪ መለሰ ዜናዊ በየአምስት አመቱ
ሕዝብ ሦስት ጊዜ በቀን እንዲመገብ እናደርጋለን ካለ ዘመናት ተቆጥሯል። በምትኩ ያየነው አገሪቱ አሁንም የምግብ እርዳታ ከሚያገኙ አገሮች የመጀመሪዋ እንደሆነች ነው። “ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ አሁንም ምጽዋት ተመልካች አገር ሆና እያለች ያገር መሬትን ለባእዳን በመቸብቸብ ላይ ይገኛሉ።

ይህን የምግብ እርዳታን አስመልክቶ ባለፈው አመት (2010) ብቻ 700,000 ቶን እህልና 1.8 ቢሊዮን ፓውንድ የገንዘብ ድጎማ ተደርጎላታል። ይህ በልመና እህል ያስቀጠለ ሕዝባችን ኑሮ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አገር በመቁረስ፣ በማፍረስ የሚታወቀው የመለሰ ዜናዊ መንግስት በ $240 ያሜሪካን ዶላር 2500 ስኩየር ማይል ድንግል መሬት ለውጭ አራሾች በመሸጥ ላይ ይገኞል። በዚህ የመሬት ችብቸባ 36 አገሮች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ሳውዲት አረብ፣ ኩዌት፣ ፓኪስታንና ሕንድ ቅድሚያ ቦታ ይዘዋል። በወርልድ ባንክ መሰረት በዚህ እርካሽ የመሬት ሽያጭ ወይንም ክራይን አስመልክቶ እንደገለጸው፤ 35 ሚሊዮን ሄክታር ድንግል መሬት ለ 36 አገሮች በሽያጭ መልክ የተከፋፈለ ሲሆን፤ Friends of the Earth የተባለ የመሬት ብክለት ተከላካይ ማህበር ደግሞ የአለማቀፍ ባንክ የጠቀሰው የመሬት ሽያጭ ዝቅተኛ መሆኑን ብሎም በጋንቤላ ድንግል መሬትና በእጸዋት ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ ለአገሪቱም ሆነ ለአለም አቀፍ የአየር ለውጥ ድንገተኛ አደጋ ነው ሲል ይገልጸዋል። ይህ በየትኛውም የአለም ክፍል ያልታየ የሕዝብ አንጡራ የተፈጥሮ ሐብትን አሳልፎ የመስጠት ድራማ በወያኔዋ ኢትዮጵያ መታየቱ አለምን ያስገርም እንጅ ለእኛ አዲስ እንዳልሆን ግልጽ ነው። በዚህ የመሬት ሽያጭ ተጠቃሚ አገሪቱና ሕዝባችን እንዳልሆነ የሁሉም ልቦና የሚያውቀው ሲሆን፡ መለስና ጠባብ ቡድኑ ሂሳብ ሳያወራርዱ ሊሄዱ እንደሚችሉ ልባቸው ስላወቀ ከዘረፋው ባሻገር አገር ለባእዳን መሸጣቸው፤ ገቢውን ወደውጭ ባንኮች ማስተላለፋቸው አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያውያን በውጭም ሆነ በውስጥ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመተቸች ብቻ ለማቆም ስለማይቻል። በአንድ መነሳት፤ በሰሜን አፍሪካ እየተካሄደ ያለውን አብዮት ወዳገርም ማስገባትና፤ አለም ጀሮ ሰጦ ባለበት በዚህ ወቅት ለለውጥ መነሳት ይገባናል። ይህንም የመለስ/ሕወሐትን ቡድን የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ የተሰብሰቡ ጥሪ አበባ ይዘን ሳይሆን አሳፍረን ልንመልሰው ታሪክ ግድ ይለናል። አገር እየፈረሰች ካፍራሽ መተባበር ያውም ለግል ህይወት መሻሻል ሲባል በእጅጉ ከወንጀለኛው በላይ የከፋ ተግባር እንደምንሰራ ማወቅ ይኖርብናል። ለዚህ ስብሰባ ተባባሪ አንፋሽ አጎንባሾች አሁንም ጊዜ ስላለ ከወገን ጋር መቆም ይኖርባችኋል። “ድመት በበላ ዳዋ ተመታ” እንዳይሆን እንመክራለን።

በዚህ የጠባቡ ቡድን የእንሰብሰብ ዘመቻ ዳላስ ከዚህ አንዱ ከተማ በመሆኑ በአፕሪል 9, 2011 ስብሰባ ተጠርቱል። ዳላሶችም ዳግም ልናሳፍር ቃል ገብተናል። ከመወቃቀስ እንድንድን ግን ይህን የዘረኞችና አጃቢወቻቸው ጥሪ ማንም ኢትዮጵያዊ እንዲቃወመው በበኩላችን በኢትዮጵያ ራዲዮ እንዳሳሰብነው በድጋሚ ሁሉም ከሕዝብ ጎን እንዲቆም፣ ሁሉም ይህን የፕሮፖጋንዳ ዛመቻ ለማምከን ተባብሮ እንዲነሳ ጥሪ እናደርጋለን። አይሆንም ብሎ ወደስብሰባ የሚሄድ ውርድ ከራስ ሊል የገባል። ስሜ ጠፋ ምስሌ ተበተነ ብሎ እንዳይናደድ ማሳሰቢያችን ለዳላስ ወገኖቻችን እንዲደርስ ይሁን። ቅዳሜ ማርች 26, 2011 በዳላስ ከተማ በአገር ወዳድና የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊወች ተሰብስበው ባሳለፉት ውሳኔ። የመጭውን የ አፕሪል 9 ስብሰባ መካፈል የማያስፈልግ መሆኑ፣ ይህ አሸባሪ መንግስት ዜጎችን በጠበንጃ አፈሙዝ በሀይል እየገዛ ባለበት፣ አገርና አንጡራ የተፈጥሮ ሐብታችን  እየተሸጠ ባለበት ሁኔታ እንድናወግዝና አሳፍረን እንድንመልሰው እንጅ እንድንተባበረው አያስፈልግም በሚል፣ ሁሉም ተስማምቷል። ይህ ጥሪ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ፣ ዘር፣ ሐይማኖና ማነኛውም የግል ጉዳይ ሳይነጣጥለን ባንድ እንቁም እንላለን።

ከመላ አገር ወዳድ ወገኖች የተላለፈ ጥሪ
ዳላስ/ቴክሳስ ማርች 28/2011

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!  

Wednesday, March 16, 2011

Judgement comes from experience, and experience comes from bad judgement. (Simon Bolivar)

ዘመነ አብዮት

በአገራችን ሕዝባዊ አብዮት ተነስቶ አንድ ስርአትን ቀይሮ የተነሳበትን አላማ ግብ ሳያደረስ በሁለት ተከታታይ ቀማኞች ተጠልፏል። ለአለፉት ሦስት ወራት እየተናጠ ያለው የሰሜን አፍሪካ ሕዝባዊ አብዮት ግን የት ሊቆም እንደሚችል ገማች የለም። መቸም አንባገነኖች የመጨረሻዋ ሰአት ደርሳም ይበቃልን አያውቁምና ሞሐመድ ጋዳፊ አሁንም የስልጣን ዘመኔ ይቀጥላል በሚል የእንቢተኝነት አመጽ ተሰማርቶ ሕዝብን እየፈጀ ነው። የጋዳፊ ጭፍጨፋን ድፍን አለም በመቃወም ላይ መሆኑንና አይቀሬ ውድቀቱ ጥይት በተኮሰ ቁጥር መቃረቡን ከሱ በቀር ለአለም ገሐድ እየሆነ መጧል። አሁን አሁን እየገረመኝ የመጣው የሌሎቻችሁን አላውቅም እነዚህ አንባ ገነን የሚባሉና የሆኑ ሁሉ ከአንድ እናት የተፈጠሩ ይመስል ባሕርያቸው ተመሳሳይ ሆነብኝ።፡ተቃውሞ ሲነሳ ለኔ ይደርሳል የሚለውን ፈጽሞ አይታሰባቸውም። ደግሞም ያች ቀን ደርሳ የመውጫ በራቸው ተበርግዶም ሰው መግደልን፤ ንጹሐንን መጨረስን ይሁነኝ ብለው ያረጉታል። አጉስጦስ ፔኖቸ ሞት ከደጃፉ ቆሞ እየጠበቀው አንድም ሰው አልገደልሁም በማለት እስከ ፍርድ ቤት ደረሰ። ከሰማኒያ አመት በላይ የሆነው ፋሽስት ፔኖቸ ለንስሐ የሚያበቃ አጋጣሚና ግዜን አግኝቶ ሳይጠቀምባት፤ ከደጃፉ ቆሞ ይጠብቅ የነበረው ሞት one way ticket አስይዞ ወሰደው። መንግስቱ ሐይለማሪያም የስደት ኑሮ እየኖረም፤ አገርና ሕዝብ እንደጎዳም ልቦናው እያወቀ አሁንም ትንኝ እንኳን አልገደልሁም እንዳለ የንስሐ ግዜውን ባልባሌ እያሳለፋት ነው።

ነገርን ነገር ስላነሳው እነኝህን የታሪክ አተላወች ጠቀስሁ እንጅ፤ ለነገሩ ያልተቋጨው ያገራችን የየካቲት አብዮት ዳግም ሊዳስሠን እየከጀለ ለመሆኑ በሰሞኑ የአርባ ምንጭ የሕዝብ መንቀሳቀስና በአዋሳም ያለለው ግር ግር ሌላ ምልክት መሆኑ አይቀሬ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረኛና ጠባብ ብሔርተኛ አናሳ ቡድን ላይገዛ በምርጫ 97 እንዳሳየ ሁሉ፤ ዛሬ በከባቢ ጎረቤቶቹ የተካሄደውና እየተካሔደ ያለው የአልገዛም ባይነትና ጀግንነት ልቡን እያሸፈተው ለመሆኑ ጥርጥር የለም። የሚጠራጠሩ ቢኖሩ የዚህ ዘረኛ መንግስት ሹንባሾችና እናገኛለን ብለው በመንደፍደፍ ላይ ያሉት አዲሶቹ ተስፈኞች ብቻ ናቸው። አሁንም ነገርን ነገር ያነሳዋልና አንድ ከዳላስ የሄዱ አገር ጎብኝ በሌላ እስክንመለስበት ስማቸውን ማንሳቱን ስላልፈለግን አንባገነኑን ስርአት በማወደስ “ከዚህ የተሻለ የለም። መቸም ከሰማይ መና አይወርድልንም” በሚል አባባል ከጎናችው የተቀመጡ ቢጤወቻቸውን ሳይቀር ያስደነገጠ በመሆኑ የስላቅ ሳቅ ሲስቁ አስተውለናል።
አንባገነኖች ተሰቅስቀው እስኪነሱ አያምኑምና የኛውም ትንሹ መለስ በሰሞኑ ከአንድ ሴት ወጣት ጋዜጠኛ ለቀረበለት ቃለምልልስ የሰነዘረውን ሳይ ከልክ በላይ አስደመመኝ። ልቡ ከላይ ታሽ እየፈረጠ ስልጣንን ግን ለማቆየት ያውም ሕዝብ የጠላው ሰው፤ ሕዝቡ መርጦናል ሢል ማየቴ ሁሉም አንባገነኖች ከፔኖቸ እስከ ሙባረክና መለስ፣ ለታሪካቸው ለቤተሰቦቻቸው፣ ለራሳቸው ምንም የማያስቡ እንደአህያዋ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አይነት ናቸው።

ዛሬ በሁሉም አቅጣጫ መነሳሳት በመጀመሩ፣ እዚህ ዳላስ ሁለት እንግዶች ተጋብዘዋል። አቶ ረዳ መሐሪና ዶክተር ታዬ የኢሕአፓ ዴሞክራሲያዊ አመራር አባላት ሲሆኑ። አገርቤት ስላለው ሁናቴና የተቃዋሚወች ትብብር እንዲሁም የዳግም አብዮት አይቀሬነትን አስመልክቶ ሊያወያዩን እሁድ ማርች 20, 2011 ይመጣሉ።

አቶ ረዳ ማህሪ ወይንም በሜዳ ስማቸው ፀሐዬ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ሰራዊትን (ኢሕአሰ) ከመሰረቱት ከትቂቶቹ ቀደምት ታጋዮች አንዱ ሲሆኑ 1966 ዓ.ም ከዋሽንግተን ከተነሱት የዚያን ግዜ ታጋዮች ከነ ክፍሉ ተፈራ፣ ለገሰ አጃቢ፣ አይንሸት ተፈሪ (የጀኔራል ተፈሪ ባንቲ ልጅ)፣ ሙሉጌታ ሱልጣን፣ ሙሉጌታ ዜና ጋር በመሆን ብዙወቹ ወደከተማ ሲገቡ ፀሐየና ብርሐነ መስቀል እረዳ ከሌሎች ታጋዮች ጋር በመሆን ወደ አሲንባ ተጉዘዋል። ከዚያን ያፍላ የወጣት ጊዜ ጀምረው አሁንም በትግሉ ጎራ ያሉ ታጋይ በመሆናቸው፤ ትውልድ ሊያውቅ የሚችለውንም ለማሳወቅም ሆነ ዳግም አብዮትን ለማምጣት ለሚደረገው እርብርቦሽ አይነታ የታሪክም ሆነ የልምድ ባለጸጋ አርበኛ ታጋይ ናቸው።

ዶክተር ታዬ ዘገየ ኢሕአፓ ወልዶ ካሳደጋቸው ታጋዮች አንዱ በመሆናቸው ብሎም በአመራር ብቃትና ታጋይነት ከልጅነት እስከዛሬ በትግሉ ጎራ በመገኘት የመሩ የታገሉና ያታገሉ ሰው ናቸው። አሁንም ስለመጭ ሕዝባዊ አብዮትም ሆነ የሕዝብ መነሳሳትን ለመፍጠር ለሚደረገው የዴሞክራሲ ትግል ለመወያየት ስለሚመጡ በዚህ በዳላስ የምትኖሩ ወገኖች ሁሉ ተጋብዛችኋል።

ይህን ጊዜ መጠቀም አስፈላጊ ነው። የየካቲት አብዮት ግቡን መቶ ዳግም ጭቆና የሌለባት አገር መመስረት አስፈላጊ ነው። መጭ ትውልዶች ለመብት በሚደረግ ትንንቅ መሞት መንገላታት አይኖርባቸውም።

ይህ ጥሪና ውይይት እንዳያመልጣችሁ ጥሪ ይድረስ ይላሉ አዘጋጆች።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ያቸንፋል!!!