Tuesday, January 25, 2011

The Souther Sudan people Referendum

የሱዳን መገንጠል በኢትዮጵያውያን አይን
              ከሳᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

በሰሞኑ በአፍሪካ ቀንድ በጥቅልና በኢትዮጵያ በተለየ ያለው አዲስ የመነጋገሪያ ወሬ የቱኒዚያ ሕዝባዊ አመጽና ያልተቋጨው ትግላቸው ሳይሆን የሱዳን ጉዳይ ነው። በእርግጥም ኢትዮጵያውያን ከማንምና ከምንም አገር በይበልጥ ከምእራብ ጎረቤታችን የሚያስተሳስረን ብዙ ጉዳይ አለን። ማንም ኢትዮጵያዊ የኬንያን ዘፈን ሰምቶ የሚወዘወዝ አላየንም። ለብዙወቻችን ከራሳችን ያላነሰ እንደሚወዘውዘን ግልጽ ነው። የዛሬውን አያርገውና ሱዳን በክፉም በደጉም መጠጊያችንና፣ መደበቂያችን ነበረች። ዛሬም ቢሆን ከሚሊወን የማያንስ ወገናችን በጥገኝነት የሚኖርባት አገር ናት። እኛ ለሱዳናውያን፣ እነሱ ለኛ እንደግለሰብ መልካም ፍቅር ቅርርብ አለን። በጋብቻ ወይም በወዳጅነት ለመገናኘት የጠበቀው የሀይማኖት ደንብ እንኳን አያግዳቸውም እኛንም እንዲሁ። ቢሆን ኖሮ አብሮ የሚኖር ሕዝብ እንጅ በባእድነት ተቆጣጥሮ እናንተና እኛ፤ ብሎ መኖር የለበትም ነበር። በዚያች አገር ያለፈ ሁሉ ሱዳናውያን ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ፍቅር ሊስት የሚችል የለም። በአለፈው ምእተ አመት የመጨረሻ አጋማሽ በአገራችን በተፈጠረው ሽብር ወጣት ወደሱዳን የተሻገሩት ምንም ችግር ሳይገጥማቸው ኬንያ፣ ጅቡቲና ሶማሊያ የነበሩት ግን ብዙ ግፍና መከራ ተቀብለው እንዳለፉ ይነገራል። ሱዳናውያኑ ከልጆቻቸው አፍ ነጥቀው ለስደተኛው ያጎርሱ እንደነበር በዚያ አልፈን ወደምእራብ የመጣን ሁሉ የምናውቀው ታሪክ ነው።

ይህ ሁሉ ደግነትና ትሥስር እያለ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ፖሊሲ ከአንድ ክፍለ ዘመን በዘለለ መመልከት ይገባል። በመሆኑም ከስሜታዊነትም ሆነ በእርግጥም የመገንጠል የመገነጣጠል አደጋን በአፍሪካ ህዝብ እንዲቀጥል መደገፍ ትክክል ያለመሆኑን ያክል ብሎም በአገራችን አሁንም ያልተቋጨው የመገንጠል ጥያቄንና መንበረ ስልጣኑን የያዘው አስገንጣይ ሐይል በተጠናከረ ሁኔታ ባለበት ወቅት፤ የዚህችን አንድ አፍሪካዊት ብሎም የቅርብ ጎረቤትና የባህል ትሥስር ያለንን አገር ለሁለት መከፈል ብሎም መዳከም መደገፍ በአቋም ስህተት ሊሆን እንደሚችል ማንም የሚስተው አይደለም። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ሌላው ነገር። እኛ ከወሳኙ የሱዳን ሕዝብ ውጭ የሆንን ሁሉ የፖለቲካ እስፖርት ከመጫወት ያለፈ ይህን ደገፍን ወይንም ሌላውን አቀነቀን ምንም አይነት ሚና ሊኖረን እንደማይችል ልንገነዘበው ይገባል። በባሰ መልኩ የራሳችንን ችግር መወጣት ያቃተን ሆኖ እያለ ስለሌሎች መጨነቁ የእርጎ ዝንብ እንደሚባለው ሊያስመስለን ይችል ይሆናል የሚል ስሜት ፈጥሮብኛል። ሆኖም የፖለቲካ እስፖርት የተለመደ ነውና፤ አንዳንድ ወገኖች ከሰሜን አሜሪካ የሞቀ ቤታቸው ሳይወጡ ስላገራችን ትግል በዚህ መሄድ እንጅ በዚያ መሄድ ብለው ሲከራከሩና ሲጣሉ መታዘባችን አልቀረም። ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆነና። የሱዳንን ጉዳይ አንስተን ስንጨነቅ ባለፉት አመታት ምርጫ 97 በደም ከተጠናቀቀ ማግስት ጀምረው ስለትጥቅ ትግል በመከራከር ልዩነት ፈጥሮ መራኮት የተለመደ ሆኖ፤ ክርክሩን በፓል ቶክና በተለያዩ ድሕረገጾች ባማረ ቀለም ሲተነተን ድፍን ሰባት አመታት መቆጠሩ እንደተጠበቀ ሆኖ። በዚህ የአንድ አገር ነጻነት እውን ሊሆን በሚችልበት እረጅም ጊዜ ከቤታቸው ደጃፍ ሳይርቁ ሜዳ ገደሉን የዳሰሱት የኔብጤወች ብዙ ናቸው። ያገራችን እጣ ፈንታ በእንዲህ የእሰጥ አገባ ክርክር መያዦ ለፊጥኝ ታስሮ፣ ጠላታች አሁንም በማይኮሰኩስ ሁኔታ ተዝናንቶ ባለበት ሁኔታ፤ በሌሎች አገሮች ሕዝበ ውሳኔ ገብተን ልንራኮት እንደማይገባ መገንዘብ ይኖርብናል።

ያም ሆነ ይህ ይህችን ጎረቤት አገር በተመለከተ ለሚደረግ ውይይት ዘለን ደጋፊና ተቃራኒ ከመሆናችን በፊት በማስረጃ የተደገፈ ትንታኔ እንድናቀርብ ግድ ይለናል።

ዘመነ ደርቡሽ በሱዳን

የኢትዮጵያን ታሪክ በትምህርት ቤት በልጅነት ስንማር ደርቡሽ የሚለው ቃል ከዘመናዊው አለም ካርታ ባለመኖሩ የትኛው አገርና ሕዝብ መሆኑን ሳናውቅ በክፉ አስበን ቋጥረን የያዝን ስንቶቻችን እንሆን፧ የምራብ ጎረቤታችን ሱዳን ከ1820 እ.ኤ.አ ጀምሮ ከኦቶማን ግብጽ የተባበረ መንግስት ስር ሆና እስከ ሀያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ እንደዘለቀች ይታወቃል። የኦቶማን ግብጽ መንግስት ወራሪና ቅኝ ገዥ ሆኖ የታየበት ጊዜ በሱዳን ሕብ አልነበረም። የሱዳን ሕዝብ ስል የሰሜናዊ አረባዊ ስሜት ያለው በመሆና. እስልምና ተከታይ በመሆናቸው በኦቶማን ቱርክ ላይ የተገዥና የገዥ ስሜት ያልነበር ያክል ይቆጥሩታል። 1820 እስከ 1885 ደርቡሽ ሱዳን በኦቶማን ግብጽ ስር ሆና ብትቆይም። በነዛያ የስድሳ አመታት ጊዜ ውስጥ የራሷ የሆኑ ነገስታት አንግሳ፣ የምስራቅ ጎረቤቷን ያለማቋረጥ ድንበሯን ጥሳ በመግባት ቁጥረ ብዙ ወረራወች አዳደረገች ይዘከራል። በተካሄዱት ወረራወች ሁሉ የድንበር ወረዳወች የቋራ፣ የጭልጋ፣ የመተማ፣ የታች አርማጭሆና የጸገዴ አርበኞች የጦር አፍላውን ሲቀበሉ መይሳው ካሳ በአገዛዙ ተበሳጭቶ በሽፍትነት በቆየበት የሃያ አመታት ጊዜ ሁለት ታላላ ጦርነቶችን ከደርቡሽ ጋር ማድረጉ የሚታወቅ ነው። ከሁለት ያላነሱ የደርቡሽ ጦርነት ያደረጉት ካሳ፤ ሱዳን የኦቶማን ግብጽ ገዥ መሐመድ አሊ በበላይነት በሚቆጣጠራት አገር አማካኝነት የተደረጉ ናቸው። እነዚህ ጦርነቶች የደርቡሽ ብቻ ሳይሆኖ የግዜው አለማቀፍ ሐይል የነበረው የኦቶማን ኢምፓየርና አንግሎ ግብጽ የተሳተፉባቸው ጦርነቶችም ነበሩ። በግብጽ ካዲስ ኢስማኤል መንግስት ከተለወጠም በኋላና በሱዳን የእስልምና አጥባቂው ሞሐመድ አህመድ 1870 እ.ኤ.አ ወደስልጣን መጥቶ ስሙን መሐዲ ካሰኘ ጀምሮም የቆየው የጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻን ቀጥለውበታል። ይህ ዘመቻ መጀመሪያ የጎጃሙ ንጉስ ተክለሐይማኖትን ልጅ ሰብለወንጊአልን ያስማረከና የመሐዲ ጦርም እስከ ጎንደር ደጃፍ ደርሶ የተመለሰበት አሰቃቂ ዘመቻ ሲሆን። በኋላ ጦርነቱ ባለመቋጨቱ በ1889 እ.ኤ.አ ንጉሰ ነገስት አጼ ዮሐንስ ጦር መርተው በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ባልባሌ ጥይት ተመተው በመውደቃቸው የንጉሱን እሬሳ እስከመማረክ ተችሏል።

ነጉሰ ነገስቱ በወደቁና ንግስናው ወደ አጼ ሚኒሊክ ከተዛወረ ማግስት 1889 የበርሊን ኮንፍረንስ ተብሎ በሚታወቀው አፍሪካን የመቀራመት የአውሮፓ እቅድ፤ የቀይ ባህር ባለቤትነት ያላትን ኢትዮጵያን ለአራት በመቆራረጥ ድንበር ለማካለል በተወሰነው የሶስትዮሽ ስምምነት፤ ታላቋ ብሪታንያ የአባይን ምንጭ ያካተተውን ካርታ ወደእራሷ ቅኝ ግዛት ወደሱዳን በመጨመር ተደራድረዋል። በግዜው የግብጽ የበላይ ጠባቂ እና የሱዳን ቅኝ ገዥ ስለነበረችም የአባይን ወንዝ አስመልክቶ ለሁለቱ አገሮች የሚገባቸውን በማደላደል ስምምነቶች በአንድ እጅ በሁለት ስም አስማምታለች። በቀጣይ በተደረጉ አባይን የሚመለከቱ ስምምነቶች ኢትዮያን ያልጨመረ ብሎም የባለቤትነት ሕልውናን የተጋፉ ስምምነቶች ተደርገዋል።

የአባይ ስምምነቶችና የአገሮች ድርሻ

ግብጽ 95% የመጠጥ ውሃ የምታገኘው ከአባይ ወንዝ ሲሆን፣ የሕዝብ ሰፈራዋ ሙሉ በሙሉ በአባይ ወንዝ ዳርቻ የተገናኘ ነው። ለግብጽ አባይ የሞትና የሽረት ጉዳይ መሆኑን ከጥንት መሪወች እስከነ ሳዳት በይፋ የተናገሩት ጉዳይ ነው። ሱዳን በተመሳሳይ 77% የመጠጥ ዉሃዋን የምታገኘው ከዚሁ የአባይ ወንዝ ሲሆን።
በነዚህ ሁለት አገሮች መካከል የአባይን ውሃ አስመልክቶ ተከታታይ ስምምነቶች ተፈርመዋል። የመጀመሪያው 1929 እ.ኤ.አ ግብጽ 48 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር አመታዊ የእውሃ ድርሻ ሲሰጣት ሱዳን 4 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ለመውሰድ በግዜው የሱዳን ቅኝ ገዥ በነበረችው ታላቋ ብሪታንያና፣ ግብጽ መካከል ስምምነት ተፈርሟል። ሱዳን ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጣች ማግስት 1959 እ.ኤ.አ ግብጽ 55.5 ቢ/ኪ/ሜ ሱዳን18.5 ቢ/ኪ/ሜ ሦስት አራተኛና አንድ አራተኛ ድርሻ በመቀባበል ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በቅኝ ግዛትም ዘመን ይሁን ከነጻነት በኋላ በተደረጉ ስምምነቶች ግብጽና ሱዳን በአባይ ባለሙሉ ስልጣን ባለቤቶች ሆነው እርስ በራሳቸው ከመደራደርና ለስምምነት ከመብቃት ባሻገር የወንዙን ብቸኛ ባለቤት ኢትዮጵያን የተደራደሩበትም ሆነ ያማከሩበት ሁኔታ አልነበረም።

ለአባይ መፍሰስ ምክንያት የሆኑ የኢትዮጵያ ተራሮች ያስከተሉት ጠንቅ

በግብጽም ሆነ በሱዳን ተያያዥ የሆኑ ባህሎች፣ ቋንቋና ሐይማኖት ሲኖሩ፡ ኢትዮጵያ ከአገሯ ከሚፈሰው ውኋ ባለፈ ከነዚህ አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በታሪክ የሻከረ ሆኖ ቀጥሏል። ይህን ሸካራ ግንኙነት መቸ እንደተፈጠረና ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል በኢትዮጵያውያን ስነ ልቦና እስከ ቅርብ ዘመን የሚያውቅ፣ ወይንም የሚጠረጥር አልነበረም። ሆኖም በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ያልተሰወረ የክፉ አስተሳሰብ ለብዙ ዘመን የቆየ ባላጋራነት ከተሞከሩ ወረራወችና ጥቃቶች መረዳት አያዳግትም። አባይን አስመልክቶም ባይሆን ግብጽም ሆነች ኦቶማን ቱርክ በተለያየ ዘመን በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። ጥቃታቸው በየትውልዱ አርበኞችና ሰማእታት መስዋእትነት ተከላክለነዋል። በተለያዩ ወቅቶችም ዲፕሎማሲንና አለማቀፍ ፕሮቶኮልን በሳተ ዛቻ ማስጠንቀቂያወች ተሰንዝረዋል። የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት 1980 እ.ኤ.አ "If Ethiopia takes any action to block our right to the Nile waters, there will be no alternative for us but to use force. Tampering with the rights of a nation to water is tampering with its life and a decision to go to war on this score is indisputable in the international community."
የቀድሞው የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ቡትረስ ቡትረስ ጋሊም በበኩላቸው በ 2005 እ.ኤ.አ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ልውውጥ ተመሳሳይ የማስፈራራት ሀይለ ቃል መሰንዘራቸው ይታወሳል። እኒሁ ባለስልጣን አለማቀፍ ደንብን ባልጠበቀ የአንድ አባል ሐገርን መብት በተጋፋ መልከ በመለስ ዜናዊ ደብዳቤ ብቻ በመመርኮዝ የሰማኒያ ሚሊዮኖችን አገር የባህር በር አሳልፈው በመስጠት ለአገር በቀል ከሀዲወች ገንጣይና አስገንጣይ ተባባሪና አስፈጻሚ በመሆን ለኤርትራ ከእናት አገሯ መገንጠል ድጋፍ አድርገዋል። ምንጭ Source: World Development Indicators 2006 – The World Ban

ዛሬ ሱዳን የሐይማኖት ልዩነት ባላቸው ዜጎቿ ላይ ለዘመናት በተፈጸመ በደል በተነሳ ጦርነት ከሰው ሕይወት ባሻገር ብዙ ሀብትና ንብረት ወድሟል። በተለየም የደቡባዊ ሱዳን የክርስትና እምነት ተከታዮች በአገሪቱ ህግ ሸሪያ እንዲተዳደሩም ግዳጅ ተጥሎባቸው ያነን አንቀበልም በማለትም አምጸዋል። እነዚህ ዜጎቿ በአገራቸው ከሁለተኛ የዜግነት ደረጃም ባነሰ፤ የተናቁና ምንም አይነት ከበሬታ የተነፈጋቸው ሆነው ግን አብረው እስከዚህ ዘመን ዘልቀዋል። ዛሬ ለህዝበ ውሳኔ በመብቃታቸው ምናልባትም አሳዛኙን የመለያየት ጉዳይ በሳጥን ሊወስኑ ይችሉ ይሆናል። ይህ ለማነኛው አፍሪካዊም ሆነ ለፓን አፍሪካ የታገለ ወይም ምኞት ላለው ሁሉ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። በአፍሪካ በቆዳ ስፋት በአንደኝነት ደረጃ ስትቆጠር የቆየችው ሱዳን ለሁለት የመከፈል እጣው ከደረሳት አነስተኛ ሆና መቆጠሯ አያጠራጥርም። ከሁሉም በላይ ሰሜናዊውና አረባዊ ሱዳናውያን የሰፈሩበት ምድር በሳህራ ምህዋር ስር ስለሚገኝ ምድረ በዳ ነው። የነበረው ለምና ያማረው መሬት ወደደቡባዊው ስለሆነ ይህም ሌላ የከፋ እድል መሆኑ ነው። ያልተቋጨው የዳርፉር ሕዝብ ጉዳይም እንዲሁ ገና ጊዜ የሚጠብቅ ሲሆን። ገዥወች በፈጠሩት ግፍ አገሪቱ ከመኖር ወዳለመኖር ሊወስድ የሚችለው ጎዳና ላይ አስቀምጧታል።

ከላይ እንደተዘረዘረው የሰሜን ሱዳን ዜጎች ሀይማኖት፣ ቋንቋና ስነልቦናዊ አመለካከታቸው አረባዊ በመሆኑ፤ ከግብጽ ጋር የተቆራኙ ናቸው። ሱዳናውያን ባሻቸው ለመኖር የግብጽ ፓስፖርትም ሆነ ቪዛ አይፈልጉም።

ሱዳን ኢትዮጵያን ለማጥቃት በተካሄደው የአርባ አመታት ዘመቻ በእነ እድሪስ አወቴ፣ አብደላ እድሪስ ኦስማን ሳልህ ሳቤ፣ በኋላም በከበሳ ልጆች በእነ ኢሳያስ ለተካሄደው ከኢትዮጵያ የመገንጠል ንቅናቄ ስንቅና ትጥቅም ሆነ ማሰልጠኛ ሆና በሁለተኛ አገርነት ያገለገለችው አገር ነበረች። ሱዳን የግብጽን ትእዛዝ ሰሚና አክባሪ በመሆኗ፣ በኢትዮጵያ ላይ ቋሚና ምህረት የለሽ ፖሊሲ ይዘው በጋራ ተንቀሳቅሰዋል። ከላይ በአንዋር ሳዳትና በቡትረስ ጋሊ የተሰነዘረው የሌላ ሐገርን ክብረ ነክ ዛቻ ሱዳን የቀጥታ ተካፋይ ናት። ከመቶና ሁለት መቶ አመታት በፊት የተደረጉት የግብጽ ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻወች በሱዳን ድንበር የዘለቁ ናቸው። ወደፊትም ሊመጡ የሚችሉት ኢትዮጵያን ከምድር ገጽ የማጥፋት ህልሞች እውን ከሆኑ የመምጫ ቦያቸው ሱዳን ትሆናለች።

ይህ ማለት እንግዲህ የአገራችን ምእራባዊ አጎራባች ቋሚ ጠላት ለመሆኑዋ ጥርጥር የለም ብየ አምናለሁ። ምንም እንኳን ሱዳን መጠጊያና መጠለያችን ብትሆንም። አሁንም ከሚሊዮን የማያንሱ ዜጎች የተጠጉባት አገርም ብትሆንም። ለኛ የታሰበ ክፉ ነገርን ግን ከማመንጨት ወደኋላ እንደማትል ለሰላሳና አርባ አመታት በኤርትራ ነጻነት ግንባርና በሻብያና በሕወሐት የተደረጉብን ውጊያወች ምስክሮች ናቸው። ሱዳን ወያኔና ሻብያ ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ በብረት ለበስ ተሽከርካሪወች ድጋፍ መስጠቷ የሚታወስ ነው። ባለፉት ሁለት መቶ አመታት እንዳስተማረን፤ እኛን ለማጥፋት ጥላቻ ኖሯት ሳይሆን በቋሚ ጥቅም ተቀናቃኝ በመሆኗ ነው። ኢትዮጵያ በታሪካችን የሱዳንን ድንበር አልፋ የገባችበት ጊዜ እንደሌለ እሙን ሲሆን። ሱዳናውያን ድንበራችንን ብዙ መቶ ጊዜ ዘለው ወግተውናል። የንጉሰ ነገስት ዮሐንስን እሬሳ ማርከዋል። አድባራትና ገዳማትን ወረው አቃጥለዋል። ቡትረስ ቡተረስ ጋሌ እንዳሉትም ሆነ አንዋር ሳዳት እቅጩን እንዳሳወቁት ለሁሉም ዛቻ በር ናት።

ኢትዮጵያውያን በደቡብ ሱዳን ሕዝበ ውሳኔ ድጋፍና ተቃውሞ ሊኖረን ይችላል። ሆኖም ይህ የእኛ አጀንዳ ባለመሆኑ የተካረረ ልዩነት ብለን ላይ ታች ልንልበት አይገባም። ከፊሎቻችን ሱዳን ከመቆረስም አለፎ ከምድር ገጽ ካርታዋ ቢሰረዝ ደግ ብለን የምናስብ ብንኖር ከላይ በነበሩ እውነታወች ተመርኩዘን ነው። ሌሎቻችን በአፍሪካ የመገንጠል ሂደት ውጭ የተሰራ መርዝ ነው መቆም ይገባዋል ብንልም አለማቀፋዊነታችን፣ ብሎም ፓን አፍሪካዊ ስሜታችን ነው። በአሜሪካም ሆነ በቻይና ጣልቃ መግባት ግን ብንከራከር ከጉንጭ አልፋነት አይወጣም ባይ ነኝ። በእርግጥም አገራችን አሁንም ባልተቋጨ የመገንጠል ጥያቄ ውስጥ በመኖሩም ሆነ፣ በስልጣን ላይ ያለው ጠባብ ቡድን የዚህ አላማ አራማጅ በመሆኑ።፡የሱዳንን ሕዝበ ውሳኔ እንደ አደጋ ብናየውም ተገቢ ስጋት ነው። ሆኖም የዚህች አገር ገንጣዮችም ሆኑ፤ አስገንጣዮች ምንጫቸው ሱዳን በመሆኑ፣ የሱዳን መዳከም አንድ ማጭድ ተወገደ ማለቴ አልቀረም። በቸር ይግጠመን።


No comments:

Post a Comment