ሁለተኛው ሕዝባዊ አብዮት
በአገራችን ለውጥን ስንመኝ ታሪካዊ ስርነቀል ለውጥን ለማምጣት በግንፍል የተነሳውን የየካቲት 1966 አብዮት ሳናነሳ ልናልፍ አይቻለንም። በቅድመ የካቲት የነበሩ አብዮታዊ ሁኔታወችን ዛሬ ላይ ሆነን ከተዋነያኑ ግምጋሜ ጋር ስናነጻጽር፣ ዛሬስ የተሻሉ ሕሊናዊና ድርጅታዊ ሁኔታወች አሉ ወይ ብለን እራሳችንን ልናይ እንገደዳለን።
በ1966 መባቻ የዚያ አብዮታዊ ትውልድ ታጋዮች በጊዜው እንዲህ እንደዛሬ በቅራኔ ተውጠው የእርስ በርስ ፉክቻ ላይ በነበሩበት በአገሪቱ ውስጥ ለአንዣበበው አብዮታዊ ማእበል የተለያየ ትንባየ ነበራቸው። ለምሳሌ ከአውሮፓ የተማሪ መሐበር የተወለደው መኢሶን ምንም እንኳን አገሪቱ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፋና የስራ ማቆም እንቅስቃሴወች በጎመራበት ወቅት ለውጥ አይቀሬ ነው ብሎ ቢያስብም። በአንድ በኩል ሰሜን አሜሪካ በውስጠ ድርጅት የመስመር ጉዳይ፡ በሌላ በኩል በውጭ ከኢሕአፓ ጋር በነበረው ያለመግባባት ተወጥሮ አንድ ነገር መስራት አልቻለም ነበር። በማለት የድርጅቱ መሪ የነበሩት አንዳርጋቸው አሰግድ በአጭር የተቀጨው መጸሐፋቸው ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ከፍሉ ታደሰ በጻፉት ያ ትውልድ ቅጽ 1 ፔጅ 84 አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪወች ማሕበር ፌደሬሽን ተመስርቶ የመኢሶን አባላት ስላልወደዱት በአውሮፓ ተወስነው ከፌደሬሽ ከለቀቁ በኋላ። በርሊን ላይ ብርሐነ መስቀል እረዳና ሐይሌ ፊዳ ተገናኝተው ብርሐነ በማነኛውም ጊዜ ሕዝባዊ አመጽ ሊነሳ እንደሚችል ሲጠቅስ፣ ሐይሌ በሰጠው ግምገማ፣ በ25 አመትም አይነሳም ብሎ ነበር ይላሉ አቶ ክፍሉ። ይህ የሁለቱ መሪወች ግምገማ በ1973 እ.ኤ.አ መሆኑ ነው። መኢሶን በአፍላው የአብዮት ሰአትም ቢሆን ኢሕአፓን ለምን የትጥቅ ትግል አልክ በማለት ከመወረፍ ባሻገር፣ መንቃት መደራጀት፣ መታጠቅ፣ ከሚል ካአፍ ያላለፈ መፈክር ብቻ በማቀንቀን ከደርግ እስከተባረረበት ቀን ለስርነቀል ለውጡ በጎ አስተዋጸኦ አልነበረውም ይላሉ የሚተቹት። ያብቻ አይደለም ባፈሙዝ ሐይል የአብዮቱን ፍሬ ነጥቆ ከቀለበሰው ወገን በመቆምም ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል።
የየካቲት 66 አብዮት ይዟቸው የተነሳቸው መሰረታዊ የለውጥ ጥያቄወች በዚያኑ ማግስት እራሱን ጊዜአዊ ብሎ ባሰባሰበ ወታደራዊ ቡድን ተጠልፈው እንደከሸፉና፣ አብዮታውያኑና ሕዝቡ በቅድመ አብዮት ጀምሮ የዘመሩለት የእኩልነት፣ የመብት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄወች ምኞት ሆነው ቀርተዋል። በአንጻሩ የደም ዘመንንና ቅልጥ ያለ ፋሽስታዊ አንባገነ የነግሰበት ሁኔታን ፈጥሯል። ድህረ የካቲት የሕዝብ ምኞት ቀቢጸ ተስፋ ሆኖ ሐዘንና እንጉርጉሮ የተተኩበት ነው የሆነው።
ዛሬም እንደትናንቱ አገራችን የለውጥ እርጉዝ የሆነች ናት። ዛሬም እንደትናንቱ እርሐብ ዳግመኛ በአገሪቱ ተንሰራፍቷል። ዛሬም እንደትናንቱ የኑሮ ውድነት በከፋ መልኩ ጣራ የነካበት ሁኔታ ነው። ዛሬም እንደትናንቱ ሕዝብ ተስፋው ቢስ የሆነበትና አገሪቱ ለተወላጅ ዜጋዋ የምድር ሲሆል እንድትሆን የተፈረደባት የሚመስል ሲሆን፣ ትቂት መንደርተኞች ደግሞ ከሚሊዮኖች አልፈው ቢሊዮኖችን የሚቆጥሩበት ነው።
ዛሬም እንደትናንቱ አገራችን የለውጥ እርጉዝ የሆነች ናት። ዛሬም እንደትናንቱ እርሐብ ዳግመኛ በአገሪቱ ተንሰራፍቷል። ዛሬም እንደትናንቱ የኑሮ ውድነት በከፋ መልኩ ጣራ የነካበት ሁኔታ ነው። ዛሬም እንደትናንቱ ሕዝብ ተስፋው ቢስ የሆነበትና አገሪቱ ለተወላጅ ዜጋዋ የምድር ሲሆል እንድትሆን የተፈረደባት የሚመስል ሲሆን፣ ትቂት መንደርተኞች ደግሞ ከሚሊዮኖች አልፈው ቢሊዮኖችን የሚቆጥሩበት ነው።
በ1966ቱ አብዮት ወታደራዊ ደርግ በስልጣን የነበሩትን ንጉሰ ነገስት ለማጋለጽ ቤተሰቦቻቸውና እርሳቸው በስዊዝ ባንክ ይህን ያክል ገንሰብ ዘርፈዋል በማለት ነበር የሕዝቡን እንቢታ የጨመረው። ዛሬ ቁጥረ ብዙ የመንደር ነገስታት በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በእስያ ባንኮች መጠነ ሰፊ ነዋይ ሸሽገዋል። ልጆቻቸውን በማስወጣት በአዎሮፓና በአሜሪካን የትምሕርት ተቋማት የሚያስተምሩበት ሁኔታ ፈጥረዋል። በአንጻሩ ዜጎች ልጆቻቸውን በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉበት ጊዜ ሆኗል። ይህ አገርን አይን ያወጣ ዘረፋ በነዚህ ስልጣን ላይ ባሉት ገዥወች ብቻ ሳይሆን ለነሱ ላደሩ ወሬ አመላላሾች በአውሮፓና አሜሪካ ነዋሪ ለሆኑም የትርፍ እኩል ሽርክናና ገንዘብ በመስጠት ያስነግዳሉ። መሬትና የተወረሱ ቤቶች የነጻ ስጦታ በቆአሚ ንብረትነት መልክ ይሰጣል። የአገሪቱ የንግድና የልማት ባንክ በዚሁ የዘረኛ ቡድን ሙሉ ቁጥጥር ስር በመሆኑ በውጭና በውስጥ ላሉ አጫፋሪወችና፣ ነገር አመላላሾች የባንክ ብድርን ደንብ ባላሟላ ገንዘብ በብድር መልክ በመሰጠት ሳይመለስ የውሃ ሽታ ሆኖ የሚቀረው መጠነ ሰፊ ያገር ሐብት ነው። በቅርቡ በአለማቀፉ ባንክ (World Bank) የቀረበ ግምት በየአመቱ በአንባ ገነን መንግስታት ስር ካሉ ድሀ አገሮች ከ$20-$40 ቢሊዮን ብር በአመት እየተዘረፈ በተለያዩ የአውሮፓ፣ እስያና አሜሪካ ባንኮች እንደሚቀመጥ ተጠቅሷል። አንባ ገነን ገዥወች በነዋይና በስልጣን የደነቆሩ በመሆናቸው፤ የያዙት ስልጣንና ዘረፋ ፍጹማዊ አድርገው ይቆጥራሉ። በመሆኑም ከጎናቸው አንዱ ሲወድቅና ወደፍርድ ሲቀርብ እያዩ በነሱ የማይደርስ ሆኖ ይታያቸዋል። የፊሊጲኑ አንባ ገነን ፈዲናንድ ማርቆስ ወርዶ ሕዝብ በመረጠው መንግስት ሲተካ ስልጣኑን ብቻ ሳይሆን የሸሸገውን ገንዘብ ጭምር ከአዎሮፓ ባንኮች ከወጭ ቀሪ $684 ሚሊዮን ከ1986-2003 ተመልሷል። ይህ ገንዘብ በባንኮች ተጭበርብሮና ተጎርዶ ተጎራርዶ ለአንባ ገነኑም፣ ላገርና ለሕዝብም ሳይሆን ባእዳን ከአስቀሩት የተረ ነው። የናይጀሪያው አባቻ የሸሸገው ከወጭ ቀሪ መልስ $700 ሚሊዮን፣ የፔይሩ ሞንተሲኖስ $92 ሚሊዮን፣ የሜክሲኮው ሳሊና $74 ሚሊዮን፣ ሞቡቱ ኮንጎ $6.7፣ ዱቫሊየር ሐያቲ $5.7 ሲሆን የጋቦን አሊ ቦንጎ፣ አይቬሪኮስት ሎረንት ብግቦ፣ ቤን አሊ ቱኒዚያ፣ ሙባረክ ግብጽ ገና ያልታወቀ ነው። አሁን ደግሞ የሊቢያው ጋዳፊ፣ የየመኑ አሊ አብዱል ሳላ እና የሲሪያው ባሽር አሳድ ገና ያልተጠቀለለ ጉዳይ ነው። ቀጣዩ የኛው ጉድ መለስ ዜናዊና ተከታዮቹ እንደሚሆኑ በበኩሌ አልጠራጠርም።
ለውጥ የሚሹ ሁኔታወች
ከላይ እንደጠቀስኩት ሕዝባዊ አመጽ የሚነሳው ሰፊ የቅስቀሳ ስራ በማካሔድ አይደለም።፡ወይንም ጠላት የሰራውን በጽሁፍና በሌሎች መገናኛወች በማጋለጥ ሊሆን አይችልም። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ፤ ሕዝባችን እንዲህ ካሉ የመገናኛ አውታሮችና፣ ኤሌክትሮኒክስ እንደ ፌስቡክ፣ ወይም የድህረ ገጽ ዜናወች የራቀ በመሆኑ ሲሆን። ብሶት ግን ከማነኛውም በላይ ቤንዚን ነው። ሕዝብ ቤተሰቡን ማስተዳደር ሲሳነው። ኑሮ ሲወደድ። የእቃወች እጥረትና የገንዘብ አለመኖር ዋናወቹ ናቸው። የካቲት 1966 የተወለደው እነዚህ መሰል ችግሮች ተደራርበው ሕዝብ ሊሸከማቸው ባለመቻሉ ነበር። የወሎ ድርቅ ከተሜውን መቀስቀሻ ነው የሆነው። ዛሬ 6 ሚሊዮኖች ተርበዋል። ዋጋ ንሯል። ወይንም ድሐ በልቶ አያድርም። ስራ አጥነት አገሪቱን አጥለቅልቋል። ከዚያ ብሶ የባለስልጣናቱ ንቅዘትና አድላዊ የሆነው ስርአታቸው ከምን ጊዜውም በላይ አስከፍቷል። ተቃውሞው በሌሎች ክልሎች ብቻ ሳይሆን፤ ሕወሐት ተፈጠርሁበት በሚለው ክልልም ጭምር መሆኑ ለነባራዊ አዲስ ሁኔታ ልዩ መልክ አላብሶታል። እነዚህ ሁኔታወች በማነኛውም አልባሌ ጊዜ የሕዝብ አመጽ ሊያስነሱ ይችላሉ። በሰሜን አፍሪካ እንዳየነው፣ አሁንም በመካሄድ ላይ እንዳለው፣ ብሶት ያነሳውን እምቢተኝነት ሊመልስ የሚችል ሐይል እንደሌለ ተረድተናል። ለዚህ ግን ዳግም ከከሸፈው አብዮታችን ትምህርት ልናገኝ ይገባል። መሪ ከማነኛውም በላይ ያስፈልጋል። ዛሬ ሊከተል የሚችል ፈቃደኛ ሞለቶ በተረፈበት ጊዜ አንድም እንኳን መሪ ሊሆን የሚችል ስብስብ ወይም ግለሰብ ኤሊቶቻችን ሊፈጥሩ ባለመቻሉ፤ መከራችን ቀጣይ ሆኗል። ይህን የመሪ እጥረት ባለፈው ምርጫ 1997 ተመልክተናል። ሕዝብ ለመስዋ’እትነት ቆርጦ በተሰለፈበት ጊዜ መሪ ሆነው ብቅ ያሉት የገዥው ክፍል ድብቅ ሰላዮች ነበሩ። የዩኒቨርስቲ ተማሪወች ወጠው የሕዝብ ድምጽ ይከበር ብለው ሲሰለፉ፣ በጊዜው ተራ በተራ በመውጣት እኛ የለንበትም በማለት ወጣቱን ለአደጋ አጋልጠዋል። መሪ ነን ብለው የተሰለፉት ከፊሎቹ መዳረሻቸው ሲጠፋ ትቂቶቹ በመብራት ተፈልገው ይህን አመጽ አልጠራንም በማለት የሰላማዊ አመጽ እርሾ ሊሆን ሰማእት ወጣቶችን ደመከልብ አድርገዋል።
ዛሬስ መሪ አውጥተናልን?
ከላይ የተጠቀሱት የአገሪቱ ህሊናዊ ሁኔታወች፣ ከተጨባጩ አስከፊ ሁኔታ ጋር የተስማሙበት ቢሆንም። የሕዝብ ፈቃደኝነት በሰፊ መኖሩን ባንጠራጠርም። አስተባብሮ ዳር ሊያደርስ የሚችል ሐይል መፍጠር ግን አልቻልንም። ዛሬ ተደራጀን የሚሉት ከፊሎቹ ሐይል ፍለጋ ወደ ደመኛ ጠላታችን ሻብያ ያንጋጠቱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ ስብስቦች የኢትዮጵያን ሕዝብ አላመኑም ወይንም አልተማመኑበትም። ብሎም ኢትዮጵያዊ አይደለሁም የሚሉትን ሻብያ እንደለገሳቸውም እየተስተዋለ ነው። የነዚህ ሐይሎች አገሪቱን እንደአገር ከማይቀበሉ ጋር መሰለፍ ደግሞ ከፍተኛ የሕዝብ ስጋት ፈጥሯል። የተማረው ክፍል በውጭም ሆነ በውስጥ በዝምታ ድባብ ውስጥ ወድቋል። ሕዝብን ለማስተማር ወይንም ከፉ ከደግን ለማሳየት ሳይሆን፤ ዝምታው ፍርሀት ለመሆኑ መጠራጠር አንችልም። በአንድነት ጎራ ተሰልፈናል የሚሉት፤ ምንም እንኳን ሰፊ ድጋፍ ቢኖራቸውም በግለሰባዊ ቂምና በቀል ተተብትበው አንድ ሐይል መሆን ተስኗቸዋል። ጸረ አንድነቱ ጎራ ሲጋልብባችውም፤ ድጧቸው እንዲያልፍ ተመቻችተው ይጠብቁታል። ትቂቶቹ የእርስ በእር ሽኩቻውን እንደትግል ሳይቆጥሩት አልቀሩም።
ሁለተኛው የኢትዮጵያ አብዮት
ከላይ የዘረዘርሁት ነባራዊ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ አገራችን ዳግም አብዮት አርግዛለች። ሕዝባችን ልክ እንደዛሬ 40 አመቱ ገንፍሎ በየትኛውም ጊዜ ሊነሳ ይችላል። ትንቢት ሳይሆን እውነተኛ አለማቀፋዊ ሁኔታወች ከውስጡ ጋር ተመቻችተዋልና። ለአርባ አመታት ሰጥ ለጥ አርጎ የገዛው ጋዳፊ ሊያምን የማይችለው ቁጣ ገጥሞታል። ለ30 አመት የልእለ ሐይሉ የበኩር ልጅ ሆኖ የኖረው ሙባረክ በአንድ ጀንበር ተወርውሮ ዛሬ ከሞት አልጋው ጋር ለፍርድ ቀርቧል። ዙሪያ ገብ ያለውን መዘርዘር አይገባም። በተግባር እየታዘብንነው። አሜሪካውያኑ አሊ አብዱላህ ሳልህ ሳይቀር ከድተውታል። አሊ አብዱላ በደቡባዊ አረቢያ ዋና የአልቃይዳ መናኸርያ በሆነችው አገር የመን ውክልና የነበረው ታማኝ ሰው ነበር። መሆኑ ግን ከሕዝ ቁጣ ሊያተርፈው አልቻለም። መለስ ዜናዊ ይህን አለማቀፋዊ ለውጥ ጠንቅቆ ያውቃል። ብርቱ ሐይል የፈነቅለኛል ብሎ ግን አያምንም። ያው እንደሁሉም አንባ ገነኖች ግብዝ ነውና። ምንም እንኳን እውነትነት ቢኖረውም። ወይንም የተቃዋሚው ሐይል ላለመስማማት የተስማማ ሆኖ ቢገኝም። የሕዝ ብሶት አድሮ ውሎ አደባባይ መውጣቱ አይቀሬ ነው። የሚከተለውም ሙባረክን ያስታውሷል።
በግብጽ ተመሳሳይ ሁኔታወች ነበሩ። ይህን ስል ተቀናቃኙን ጎራ አስመልክቶ ማለቴ ነው። የእስላም ወንድማማቾች ድርጅት ከ 1950 ወቹ ጀምሮ የስርአት ለውጥ ለማምጣት ታግሏል። ከግማሽ ምእተ አመት በላይ መታገሉ ግን ድል አላጎናጸፈውም። ፈጥኖ የደረሰው የአንድ ወር ሕዝባዊ አብዮት ግን ከተቃዋሚውም ሆነ ከገዥው ፍላጎትና ምኞት ባለፈ ጠራርጎት ሄደ። የኛ ተቃዋሚወችም በተለየም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉት ከወዲሁ ሕዝብን ለመምራት ካልተዘጋጁ በሰሜን አፍሪካ ያየነው በኛም አገር መደገሙ አይቀሬ ነው። ተቃዋሚ ስል በአገሪቱ አንድነትና ሉአላዊነት የሚያምኑትን ማለቴ ነው።
ሌላው የተቃዋሚወች አይነትና አላማወች
በአገራችን የተደራጁና የተዘጋጁ የአንድነት ሐይሎች የመሪ ቦታውን መያዝ ካልቻሉ፤ ብሶት ቀስቅሶት የሚነሳ ማነኛውም ለውጥ ሕወሐት/ኢሕአዴግን በሚመስሉ ሐይሎች ይነጠቃል። አገሪቱም ከሳት ወጦ እረመጥ እንዲሉ ወደ ሌላ ጠባብ ቡድን ልትሸጋገር ትችላለች። ይህ ተንባይ አይፈልግም። ኦነግና አብነግ በአገራችን ዋና ጠላት ታጅለውና ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ። አንድም ከሕወሐት (ወያኔ) የተለየ አቋም የላቸውም። በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ትግላቸው አልፋና ኦሜጋው የአቢሲኒያን (የኢትዮጵያን) ቅኝግዛት የማስወገድ ነው። ይህን አደገኛ እቅዳቸውን ሰሞኑ ከግንቦት 7 ጋር በሚያደርጉት የጋራ ሕዝባዊ ስብሰባወች በተሻለ ቋንቋ ያቀርቡታል። በአትላንታ፣ በቨርጅኒያ፣ በሐምበርግና በሎንደን በተደረጉ ስብሰባወች። ኦነግ የሚታገለው ለሕዝበ ውሳኔ መሆኑን ተደጋግሞ በአመራሮቹ ተነግሯል። ይህ ቃል በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በዶክተር ጌታቸው በጋሻውና በዶክተር ብርሐኑ ነጋም ተደግሟል።
ሕዝበ ውሳኔ ታሪካዊ ይዘቱና አመጣጡ በኢትዮጵያ
Referendum (ሕዝበ ውሳኔ) በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው በኤርትራ ሲሆን ይኸውም የተባበሩት መንግስታት ተወካዩን ልኮ ባረጋገጠው መሰረት በአውሮፓ አቆጣጠር ከማርች እስከ ሴብቴምበር 1952 ነበር። የአንድነቱ ጎራ በሰፊ ድምጽ አቸንፎም ኤርትራ በፌደረሽት ተጨመረች። ሁለተኛው በመለስ ዜናዊ ይሁንታ ነጻነት ወይንም ባርነት የሚል ሁለት ምርጫ ለኢርትራ ሕዝብ ቀርቦለት እንደአውሮፓ አቆጣጠር በ ሜይ 24፣1992 የተካሔደው አመጻዊ ተግባር ነበር።
ዛሬ ከ40 አመታት በላይ ከፊል ኢትዮጵያን ለመቁረስ የታገሉ ሐይሎችም ሕዝበ ውሳኔ ይሰጠን ሲሉ መቆየታቸው ይታወቃል። በዋና አላማነት የሚወስዱት ኦነግ፣ አብነግና የሲዳሞ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ናቸው። ትግላቸውን መሰረት አደረግን የሚሉት በጸረ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት በመሆኑ። የሕዝበ ወሳኔው አላማና ግብ ከአቢሲኒያ (ኢትዮጵያ) ቅኝ ግዛት ለመላቀቅ መሆኑን አደረጃታቸውና፣ የፖለቲካ ግባቸው ገላጭ በሆኑ ድሕረ ገጾች አሳውቀዋል። ሆኖም ምርጫ 1997 እንዳሳየን የተባሉት ድርጅቶች እንቆምለታለን የሚሉት ወገናችን በዚያ ምርጫ በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን ያሉትን የዘር ድርጅቶችን እንኳን ሊመርጥ አልፈለገም። በተቃራኒው አንድ ሕዝብ አንድ አገር በዴሞክራሲ ብሎ የተንቀሳቀሰውን ቅንጅትን መርጦ ነበር። ከላይ አሁንም የመገንጠልን ጥያቄ ይዘው የሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች፡ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ተባባሪ በማግኘታቸው በየከተሞች እየተንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያንን የማግባባቱን ፖለቲካ ተያይዘውታል። ለዚህ እንቅስቃሴ ግንቦት 7 የተባለው ድርጅት አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ እያገለገለ ነው። ሁለቱ የዚህ ድርጅት አመራር አባላት 1991 ዓ.ም ወያኔና ሻብያ እንዲሁም ኦነግ አዲስ አበባን በተቆጣጠሩበት ወቅት ከነበሩበት የውጭ አገራት ተመልሰው አገር ገብተው ነበር። አቶ አንዳርጋቸው በወያኔ አገዛዝ ተማረርሁ ብለው እስከለቀቁበት ጊዜ ድረስ ባአዴን በተባለው ድርጅት ስር ሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባም ነበሩ። ሐሜት ይባል ወይንም ለአገር መቆርቆር፣ ብዙ ወገኖች አሁን ከኦሮሞ ነጻነት ግንባርና ከኦጋዴን ግንባር ጋር የሚያደርጉት የማስተዋወቅ ዘመቻ በጥርጣሬ ይመለከቱታል። ከሁሉም በላይ ከመቶ አለቃ አያልሰው ደሴ ጋር በተደረገ ክርክር የነዚህ የነጻ አውጭ ድርጅቶችን አቋም መደገፋቸው ቁጥረ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ማሳሰቡ አልቀረም። 1991 ወያኔን ደግፈው መግባታቸው አላማውን ስለሚጋሩ መሆን አለበት፣ አሁንም ከወያኔ ተጣሉ እንጅ ከአላማው ችግር የለባቸውም የሚል እምነት በሁሉም ልቦና ገብቷል። አቶ አንዳርጋቸው ሕዝበ ውሳኔን የሚደግፉ መሆናቸውን በክርክሩ አልደበቁም። በተመሳሳይ በአሉላ አባነጋ የፓልቶክ መወያያ ዶር ጌታቸው በጋሻው ከዶክተር አረጋዊ በርሔ ጋር በነበር ውይይት የነዚህ የነጻነት ግንባሮችን የሕዝበ ውሳኔ ጥያቄ እንደሚደግፉ አስታውቅቀዋል። ሁሉም የዚህ ድርጅት መሪ አባላት ዶክተር ጌታቸውን ዝጨምሮ የአንድነት ሐይል የሚባል የለም። ቢኖርም ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም በሚል በጽሁፍና በቃል ተናግረውታል። በዚህ መልክ እነዚህ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅታቸው ወዴት እየሄዱ መሆናቸውን ለማወቅ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አይፈልግም። ባጭሩ በየአደባባዩ በኩራት ያሉበትን ሰልፍ እያሳዩ ነው። እንዴው ለግንዛቤ ግንቦት 7 ኢትዮጵያዊ ስም አልተላበሰም ይሉ የነበሩ ወገኖች፤ ጥርጣሬአቸው ቀደም ቢልም አለመሳሳታቸውን እያየን ነው።
ማጠቃለያ
ከምንጊዜውም በላይ አለማቀፍና አገራዊ ሁኔታወች ከተስማሙበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ለውጥ ባገራችን ለመምጣቱ መጠራጠር የለብንም። ሆኖም ለውጡ የማይቀር ከሆነ የለውጥ መሪና ሐዋርያ እንፈልጋለን። ያም ቢሆን በአንድ ጀንበር ሊፈጠር አይችልም። እንዳለፈው አብዮት ዛሬም ከዳር የሚጠብቅ ነጣቂ፣ ከምእራቡ ስጋት ጋር ተጨምሮ በዝግጅት ላይ ነው። ኢትዮጵያን ለማትረፍና የሕዝብ ምኞትን እውን ለማረግ ጊዜው አሁን። ለዚህች አገር የታገሉና መስዋእትነትን የከፈሉ በረባና ባረባው የሌለ ልዩነታቸውን አቁመው ይተባበሩ። አልያ ሁሉን ለመፈጸም የማይሳነው ዳግም ሁለተኛውን ወያኔ ሊተካ ይችላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!
አንድነት ሐይል ነው!!
bhunegnaw@aol.com
አንድነት ሐይል ነው!!
bhunegnaw@aol.com
No comments:
Post a Comment