Wednesday, October 6, 2010

እልም ነው፣ ጭልጥ ነው፤ ውሃ አይላመጥም። ወዳጅ ጠላት ላይሆን............የተከፋ አንጎራጓሪ

የወይዘሪት ብርቱካን ሚዲቅሳ መፈታት ውብ ዜና
ᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ

ዛሬ መስከረም 26 ቀን 2003 ዓ.ም በእምነበለ ፍርድ ለ 20 ወራት በእስር የቆየችው ታጋይ ወጣት ወ/ሪት ብርቲካን ሚዲቅሳ ከስድስት አመት ልጇና ከአዛውንት እናቷ ተቀላቅላለች። ከዘመን ዘመን ግፍ ተዘርቶ ግፍ የሚመረትባቷ ኢትዮጵያ አሁንም ባላቋረጠ የግፍ ጅረት ትንገላታለች። ወ/ሪት ብርቱካን ከሌሎች የቅንጅት አመራር አባላት ጋር በምርጫ 97 ማግስት ታስራ ሁለት አመት በእስር ቆይታ በተለቀቀች አመት እንኳን ሳይሞላ ዳግም ያለምንም ምክንያት እንደገና ወህኒ ተወርውራ ሌላ ለሁለት አመት ፈሪ ማስቆጠሯ ለሁላችንም ያሳዝናል።

ወይዘሪት ብርቱካን ለሕዝብ ልእልና፣ ለአገር አንድነትና ለዴሞክራሲ ስትል የተቀበለችው ግፍና መከራ ለተከታይ ትውልዶች አኩሪና አንጸባራቂ ገድል ነው እንላለን።

ወያኔ/ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የአገሪቱ እስር ቤቶች አፋቸውን ከፍተው ሳይሆን የጠበቁት በንጹሀን ተሞልተው ነበር ያገኛቸው። ከሊቁ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ በዘመነ ወያኔ በየከተማው ያሉና የነበሩ ህጋዊ እስርቤቶች ሞልተውና ተትረፍርፈው፤ ተጨማሪ ማጎሪያ ካምፖችን ጨምሮ በአስርና በመቶ ሽሕወች የሚቆጠሩ ዜጎችን አጉሯል። ወይዘሪት ብርቱካን የህግ ትምህርቷን አጠናቃ በአገሯ የዳኝነት ሙያ ተሰማርታ ስታገለግል ከቆየች በኋላ፤ ዘረኛው መንግስት በዜጎች ላይ በሕግ ስም የሚካሄደውን ወከባ፣ እስራትና ግድያ በአይኗ አይታ፣ በእጇ ዳሳ በመገንዘቧ፤ ኢፍትሀዊ ስርአት ባለባት ኢትዮጵያ የዳኝነት ወንበሯን ይዛ ለመቆየት ሕሊናዋ ስላልቻለ። የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሰላም አገር ውስጥ ከሚታገሉ ሐይሎች ጋር ተቀላቅላ አኩሪ ገድል አስመዝግባለች።

ወይዘሪት ብርቱካን ታዋቂና ምርጫ 97 ከወለዳቸው ታጋይ ወጣቶች አንዷ በመሆኗ። የእሷን በግፍ መጋዝ አስመልክቶ በውጭና በአገር ውስጥ ከፍተኛ የትፈታ ትግል ተደርጓል። የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶችም ሆኑ፤ የወያኔውን መንግስት እንደግፋለን የሚሉ መንግስታት ይህን የእሷን መታሰር አስመልክቶ በሰበአዊ መብት ተሟጋቾች ይቀርብ የነበረውን የትፈታ ጥያቄ ችላ ሊሉት አልቻሉም። በመሆኑም የወያኔውን መሪ መለሰ ዜናዊን መጎትጎታቸው አልቀረም። በቅርቡ በኒውዮርክ የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ጉዱን መለስ ዜናዊን በጋበዘበት ወቅት ለዩኒቨርስቲው ፕሬዜዳንት ያጋጠመው አለም አቀፍ ጩኸት የዚህ ግፊት አንዱ አካል ነበር። መለስ ኮሎምቢያ በመጣበት ወቅት ከኢራኑ ፕሬዚዳንት አህመዳጃድ የበለጠ ተቃውሞ በአዳራሽ ውስጥም ሆነ በግቢው እንደደረሰበት ታውቋል። ይህን ግፊትና ሐፍረት ለመሸፈን ሲል ታጋይዋን ይቅርታ ጠየቀች ለማለት ተገዷል። ብርቱካንን ከመፍታት አዜብን መፍታት ይቀለኛል እንዳላለ። የአለማቀፍ ግፊትና በየሄደበት ያጋጠመውን ወከባ መቋቋም ግን ሊሆንለት አልቻለም። ትግሉ ይቀጥላል። በእየእስር ቤቱ አሁንም በግፍ የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን በመደገፍ አለማቀፋዊው የተቃውሞ ሰልፍና አቤቱታ ይቀጥላል። 80 ሚሊዮን ሕዝባችን ነጻ እስኪወጣ ቀጣይ ትግል ከፊት ለኢትዮጵያ ታጋዮች በውስጥም በውጭም ይጠብቃቸዋል።

ለዚህች አገር ክብር፣ ለሕዝቧ ነጻነትና ለሕግ የበላይነት ሲሉ የትናንት አንባገነኖችን የታገሉ የወያኒንም ዘረኛና ጠባብ መንግስት በመታገል ላይ እያሉ ዳብዛቸው የጠፋ አያሌ እውቅ የትውልዳችን ታጋዮች ዛሬም ከእስር አልተፈቱም። ወያኔ የኢሕአፓ መሪወችንና ታጋዮችን የት እንዳደረሰ እንኳን አልተነፈሰም። እነዚያ ታጋዮች ዛሬም በወያኔ የጉድጓድ እስር ቤት ባዶ ስድስት በሚባል በትግራይ ክፍለሀገር በተሰራ፤ ወያኔወች በረሐ በነበሩበት ጊዜ ለአገር ተቆርቋሪ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን አሰቃይተው የፈጁበት እስር ቤት ዛሬም ላገር አንድነት፣ ለሕዝብ እኩልነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ በማለት ግንባራቸውን ባላጠፉ ታጋዮች ተሞልቷል።

ታጋይዋ አበራሽ በርታና፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጀምሮ 1956 ዓ. ም በትግሉ ጎራ ተሰልፎ የወጣት እድሜውን በበረሀ ያሳለፈው ጸጋዬ ገ/መድሕን (ደብተራው) ይስሐቅ ደብረ ጺዮን፣ ተስፋየ ከበደ፣ ስጦታው ሐሰን፣ ወንዱ ሲራክ፣ አበበ አይነኩሉና ሌሎች ታጋዮችም ላለፉት 20 አመታት በጉድጓድ እስር ይገኛሉ።

አቶ አበራ የማነአብ በ1994 እ ኤ አ የአማራጭ ሐይሎችን የሰላምና የእርቅ አላማን ይዞ አዲስ አበባ በመጓዝ ከቦሌ ያውሮፕላን ማረፊያ ተይዞ ላለፉት 16 አመታት በእስር ላይ ይገኛል። ይህን ታጋይ ዜጋ የወያኔው ፍርድ ቤት እንኳን ፈቶ ካሰናበተው በኋላ በመለስና ተባባሪወቹ መልሶ ወደእስር እዲወረወር ተደርጓል።

ወያኔ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በደቡባዊና በምስራቅ ክፍለሐገራት ከትውልድ ትውልድ የኖሩ ዜጎችን፣ በነፍጠኝነት፣ በትምክሕተኝነት በመወንጀልና፤ ነዋሪውን በመቀስቀስ፤ ወገኖቻችን በገደል እዲወረወሩ አድርጓል፣ አስደርጓል።

ይህን ግፍ የተቃወሙት ታዋቂው ሐኪም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ለምን የሕዝብ ግፍን እያዩ ዝም አላሉም በሚል ቂመኛና በቀልተኛ በሆነ የወያኔ ሴራ ተይዘው በእምነበለ ፍርድ፣ ሕክምና እንዳያገኙ በመደረግ ለሞት ተዳርገዋል። ታጋዩ ግንባራቸውን ሳያጥፉ ከዘረኛ ወያኔወች ምንም አይነት የይቅርታ ቃል ሳይተነፍሱ ሕይወታቸውን አሳልፈዋል። ወያኔ በዘረኝነት ተወልዶ በዘረኝነት ያደገ ቂመኛ ድርጅት በመሆኑ። አላማ ተግባሬ ብሎ ትግል ሲጀምር በጸረ አማራነት ሲሆን። ያባሕርይው ስልጣን ከያዘ 20 አመታት በኋላም አልበረደም። አነጣጥሮ የተነሳበትን አላማውን አገር በመቁረስና ለባእዳን በመቸብቸብም የቂምና የበቀል ቋያው መግለጫ ሲሆን አሁንም ድረስ አልበረደለትም። ዛሬ ያሰበው ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ሊጠፋ ባለመቻሉ። የእውር ድንብሩን ከወዲያ ወዲህ በመምዘግዘግ፤ በኦሮሞኛ ተናጋሪ ዜጋ ላይ የከፈተው ጦርነት በአስርና በመቶ ሽሕወች ወደእስርና ስደት ወርውሯል። ትናንት በአማራ ሲዘምት ዝም በመባሉ ዛሬ በኦሮሞ ወገን በኦነግነት እየከሰሰ ሲዘምት አናጥሎ የማጥቃት ስልት መሆኑን መገንዘብ ይገባል እንላለን።

ላለፉት ሰባትና ስምንት አመታት ኦሮምኛ ተናጋሪ ዜጎች ያለምንም ወንጀል ከየቀያቸው እየታደኑ በቃሊቲ፣ በሸዋ ሮቢትና በሌሎች ማጎሪያ ካምፖች በመታጎር በሽህወቹ የሚቆጠሩ ዜጎች በተስቦ በሽታ እንዲያልቁ ተደርጓል።

ይህን አይን ያወጣ ግፍ፣ በዜጋና ባገር ላይ የሚፈጸም ወንጀልን እንደትክክለኛ በመቁጠር ከጎኑ የቆሙ ሁሉ ሳይመሽ መገልበጡን ቢያውቁበት ምንኛ ባማረባቸው ነበር።

አለም ያወቀውን የጥቁር ዘረኛ ምግባረ ብልሹ መንግስት፤ አንዳንድ ግለሰቦች ሀብትና ንብረት እናገኛለን በማለት ደጋፊ ሆነው ስናይ፤ መለሰ ዜናዊን እንደመላክ ለማቅረብ ሲዳዱ ስንታዘብ በሐፍረትና በሐዘን ነው። ላለፉት 20 አመታት በሕዝባችን ላይ የወረደውን ግፍ የአገር መቆረስና የባእዳን መሰጠትን፤ የሐይማኖቶችን ግጭት ማራገብን ላንድም ቀን ያልኮነኑት የእምነት ቤታችንን እንዲመሩ ተሿሚውን አባ ጳውሎስንም የሚደግፉ ብጹሕ ናቸው ተቀበሉ ብለው የሚያስገድዱንንም ስናይ እንዲሁ በትዝብnና በሐዘን ነው።

ለሁሉም ዛሬ የወይዘሪት ብርቱካን መከራ ባያልቅም። ከጠባቧ የማጎሪያ ቦታ መውጣቷን ስንሰማ፤ ጡቷን ለተነጠቀችው ቃሌና ለደካማ እናቷ እንኳን ድስ ያላችሁ እንላለን። የሁሉንም በግፍ የታሰሩ። ለአመታት በባዶ ስድስት የጉድጓድ እስር ቤት ለተወረወሩ፤ ለነ አበራ የማናብ፣ ጸጋዬ ገ/መድሕን፣ ስጦታው ሐሰን፡ ወንዱ ሲራክ፣ ተስፋየ ከበደ፣ አበበ አይነኩሉ፣ አበራሽ በርታ እና አእላፍ መከራ ተቀባይ ወገኖቻችን ሁሉ ነጻነት እንድንታገል እናሳስባለን። አፋቸውን ከፍተው የሚጠብቁት የቃሊቲ፣ የሸዋ እሮቢት፣ የጊቤ፣ የትግራይ የጉድጓድ ማጎሪያወች ሁሉ የሚዘጉት ዘረኛውና አንባ ገነኑ ወያኔ ሲወገድ ነው። ለዚያም አሁንም ትግል አሁንም ድጋፍ ይጠይቃል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

No comments:

Post a Comment