ታሪክ አንድ በሁለተኛ ዙር ስትጎበኘን
ሳᎀኤል ሽፈራው/ዳላስ
ዛሬ አካባቢያችንን በተመለከተ ትንሽ ልንል ተነስተናል። ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ ዛሬ በዚህ በዳላስ ፎርትወርዝ አካባቢ የምናየው ሁኔታ ወያኔ ባህርዳርንና ጎንደርን በያዘበት ወቅት የነበረውን ደጋሚ ሆኖ ስላገኘነው ባይገርመንም የተዋንያኑ ምሥል ግን ድባብ ሰጥቶናል።
ነገሩ እንዲህ ነው። ያኔ በ1989-90 እ.ኤ.አ አንድ መድረክ የሚባል ስብስብ በአገራችን አንዣቦ በነበረው አደጋ ዙሪያ ሁሉንም ዜጋ አገናኝቶ ሊያወያይ የሚችል በሚል ይፈጠራል። ይህን መድረክ በጊዜው ለመጠቀም የታሰበው አገራችን ወዳጅ አልባ በመሆን፤ ምእራባውያኑ ከከባቢ የአረብ መንግስታት ጋር በመሆን የታሰበውን የሰሜን ግዛቷን ገንጥሎ ለመስጠት የተረባረቡበት ጊዜ በመሆኑ። በአገር ውስጥ አለሁ ይል የነበረው የመንግስቱ ሐይለማርያም አንባገነን መንግስት ከወዳጁ የሶቭየት ሕብረት ተለያይቶ ብቻውን የሚንጠራወዝበትና ሕዝቡ በጦርነት የሚናጥበት ብሎም የሰሜን ተገንጣዮች በድል አድራጊነት የሚገሰግሱበት ወቅት ስለነበር። በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ከአገሩና ከሕዝቡ ጎን እንዲቆም ለማስተባበር ታስቦ ነበር የተመሰረተ። ውሎ ሳያድር አንዳንዶች አጥንትና ደም ቆጥረው ለሕዝብና ለአገር ሳይሆን በመገስገስ ላይ ለነበሩት ሊያግዝ የሚችል እርምጃወች መውሰድ ጀመሩ። የለም ይህ አይሆንም። ላገር ለወገን የሚጠቅም አይደለም በሚል በዚያ የአመራር ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ ቢሞክሩም ድምጻቸው በብዙሀኑ ተዋጠ። ትቂቶቹ እንዴውም ሚዛን በማየት ድምጽ ሰጭ ሆነው አረፉትና የወያኔና ሻብያ ደጋፊወች የበላይነቱን ወሰዱ።
በዚያ አስቸጋሪ ወቅት፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ መታፈን በውጭ ለድል አድራጊወች አንፋሽ አጎንባሽ መባዛት በጊዜው ለቁርጥ ኢትዮጵያውያን ተስፋ አስቆራጭና አሳዛኝም ነበር። አገር ወዳድ ነን ይሉ የነበሩ እዚያ የወያኔ፣ ሻቢያ፣ ኦነግ ደጋፊ ከነበሩትና ብዙሐን መሆን ከቻሉት ጋር ድምጽ በመስጠት ለታሪክ የማንረሳው በጊዜው ወያኔን ከአሜሪካን መንግስት ጋር አገናኝ የነበሩትን ዶክተር ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴን በእንግድነት ጋበዙ። አይሆንም ብሎ የተከራከረ አንድ ድምጽ እንደነበር ዛሬም የዚያን ጊዜ የውይይት ሚኒት ከጃችን አለ።
በሚቀጥለው የኦነጉን አመራር፣ ከሻብያ የውጭ ግንኙነት ዋና ሐላፊ ጋር በመጨመር አንድ ኢትዮጵያዊ ዶክተር መስፍን አረያን አካተው ስብሰባ ተጠራ። ዳግም ውርደት እንዲሉ ዶክተር መስፍን አርያ በሁለቱ ተቧዳኝ ጸረ ኢትዮጵያ ምሁራን ተሰደበ። ኢትዮጵያውያን ተጠርተው ተሰድበው ወደቤታቸው ተመለሱ። ወደስብሰባው የመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ከወያኔ፣ ሻቢያ፣ ኦነግ ጥምር ደጋፊወች በቀር ስብሰባውን ጥለው ሄዱ።
በኢትዮጵያ ስም የተቋቋመ የውይይት መድረክ ለጠላት አንባሳደር ሆኖ ሲያገለግል አይተናል። ያኔ ያገሪቱን አንድነት እንደግፋለን ያሉት ድምጽ ለጸረአንድነቶች እንደሰጡም ታዝበናል። ዛሬ ዳግም በተመሳሳይ ተዋንያን የዚያን ጊዜ ጉድ እየተደገመ ስናይ እንዴት በሁለት አስርት አመታት በተመሳሳይ ተዋንያን ታሪክ እራሷን ደገመች ማለታችን አልቀረም።
በአሁኑ ጊዜ የአማራ ልማት ማሕበር (አ.ል.ማ) ስር ተደራጅተው ኢትዮጵያውያንን በዚህ ድርጅት ስር ለማሰባሰብና እጅ እንዲሰጡ ደፋ ቀና የሚሉት፣ ሌላውን በተለየም ይቃወመናል ብለው ያሰቡትን ሁሉ እየጠሩ መጠየቅ እንደጀመሩም ስንሰማ ታዝበናል። አልፈው ተርፈው በወያኔ ተዘይዶ የቀረበልንን ድርጅት የሚቃወሙ ሁሉ ፖለቲከኞች ናቸው ሲሉም ይደመጣሉ። ፖእለቲካ ያውም የዘር በጠላት የታሰበና የተደራጀ እየሰሩ ለአገር ተቆርቋሪ የሆኑ ወገኖችን ሁሉ ፖለቲከኛ ማለት ለማደናቆር እንደሆነ ለኛ ግልጽ ነው። ታሪክ እራሷን ትደግማለች ያልንም ለዚህ ነበር። ያኔ ወያኔን፣ ሻብያን እና ኦነግን እየደገፉ ለአገር ለወገን ተቆርቋሪ ወገኖችን ፖለቲከኞች ብለው ያሳጡ እንደነበር ይታወሰናል።
ተመሳሳይ ግለሰቦች ትናንት ጸረ ኢትዮጵያ ሐይሎችን ደግፈው ዛሬ ደግሞ ወደ መለስ በመጠቃለል አ.ል.ማን መስርተው እየተንቀሳቀሱ ስናይ ዳግም ታሪክ መሰራቱን በትዝብ እያስታወስን ነው። ኦ.ነ.ግ ዛሬ እንደያኔው ከወያኔ ጋር ባለመሆኑ እነዚያ ደጋፊወቹ አሁንም ይደግፉት ወይን ይቃወሙት አናውቅም። ሆኖም ያው ከመሀበሩ ያልተለዩ መሆኑን ግን አስተውለናል።
ወያኔ/ኢሕአዴግ ከምንጊዜውም በተሻለ ከፍተኛ የመንቀሳቀስና የመደራጀት ሙከራውን በውጭ ቀጥሏል። በዋሽንግተን ዲሲና በኒውዮር የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎች ከምንም የመጡ አልነበሩም። በከተማችንም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እየተካሔደ ነው። ለአመታት የተገነቡ፣ የተደራጁ ተቋማትን በውድም በግድ ለመንጠቅም እየተካሄደ ያለው ሴር ላለማየት ላልፈለጉ ይደበቅ እንደሁ እንጅ። ገሐድ የወጣ ያደባባይ ሚስጥር ሆኗል።
በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ ከተሞች በውጭ ፋይናንሱ ሞሐመድ አላሙዲን አማካኝነት የኢትዮጵያውያን ተቋማት እንደ የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌደሬሽን፣ ኮሚውኒቲና አብያተ ክርስቲያናትን ለመንጠቅ ወይም በሰላም በቁጥጥር ለማስገባት የሚደረገው ደባ አሉባልታ ሳይሆን ገሐድ እንቅስቃሴ ነው። ተስፋ ቆራጮችም በዚህ ተግባር ደባል መሆን ሲዳዱ፣ ለአንባገነኑ መለስ ላሜ ወለደች እንዲል ሆኗል። ይህ ተንኮለኛና መሰሪ አንቱ የተባሉ በእድሜም ሆነ በኑሮ መልካም ሁኔታ ላይ ያሉትን በተለያየ መልክ ወደሱ ለማስገባት ሁኔታውም አጋዥ ሆኖ አግኝቶታል። ዛሬ አትልፉ የወያኔ መንግስት አይነቃነቅም። አርፋችሁ ተቀመጡ የሚለው በአንድና ሁለት መጨመሩን ስናይ በትዝብት እንጅ በብስጭት እንዳልሆነ ይታወቅ። ምክንያቱም እውነት የማታ ማታ አሸናፊ ናትና።
የኛን ጩኸት ነጥቀው ተበደልን ሲሉ። በኛ ላይ ፖለቲካ ያውም የዘር እየሰሩ፣ ለሰበአዊ መብት፣ ለእኩልነት፣ ለአገር አንድነት የሚቆረቆሩ ወገኖችን ፖለቲከኞች ሲሉ ስንሰማ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እዲሉ ተቸግረናል። እነኝህ ልብ አውልቅ ግለኞች እነሱ በልተው እስካደሩ፤ ሌላው ቢደፋ ጉዳያቸው እንዳልሆነ እውቅ ስራቸው አሳይቶናል። ከአናሳው የመጡ ጠባቦች ሰጥ ለጥ አርገው ያለልዋጭ እየገዙ ተዋቸው ሲሉ፣ ያዛኝ ቅቤ አንጓች መሆናቸውን ያሳዩናል። በየ አራት አመቱ በሚለወጥ የሕዝብ ውክልና ባለውና በገለልተኛ ዳኝነት በጋራ ሕገመንግስት በሚተዳደር አገር እየኖሩ መለስ ለዘላለም ይግዛ ይሉናል።
ታሪክ እራሷን ትደግማለች እንዲሉ በየከተሞችና በዚህ በምንኖርበት ቀበሌም ከ 20 አመታት በፊት ያየነውን ሲደገም በመታዘባችን እንሆ ታሪክ አንድ ሌላ ዙር በተመሳሳይ ተዋንያን አብስራናለች። ለሁሉም ሕዝባችን ዴሞክራሲ ይፈልጋል፣ እኩልነትና ፍጹም ነጻ ሆኖ እንዲኖር ይመኛል። ሕዝባችንና አገራችን የቅድመስልጣኔ ቁንጮ እንጅ እንደሌሎች የአውሮፓ ቅኝ ገዥ የፈጠረን አይደለንም። በነጻ የመኖርና የማለፍ መብቱ እንዲከበር ላለፉት አርባ አመታት ታግሏል። እውን እስኪሆንም ትግሉ ይቀጥላል። ዴሞክራሲ አይሆንህም የሚሉትን፣ ነጻነትን መለስ ሰጠህ የሚሉትን ለታሪክ ብሎ ትግሉን ይቀጥላል።
መልካም ሰንበት
No comments:
Post a Comment