አስቸጋሪው ወር በአዲስ ፍልሚያ ሲተካ
በዚህ ባሳለፍነው የህዳር ወር ብዙ ነገር በመላ አለም ተመልክተናል። በተለየም አገዛዙ በአገርቤት ያለውን የአፈናና የእመቃ ስርአት በአስተማማኝ መቆጣጠሩን በማረጋገጥ በውጭ የሚኖረውን ስደተኛ ዜጋ ለመግጠም መነሳቱን አመላካች የሆኑ ኩነቶችን ተመልክተናል። ሆነም በእርግጠኝነት ለመናገር ይህ በአገርና በህዝብ የተጠላና የተናቀ ዘረኛ ስርአት የጊዜ ጉዳይ እንጅ ማለፉና መሪወቹም በአገር ማጥፋትና በአገር ክህደት መጠየቃቸው አይቀሬ ነው። ወያኔ/ኢሓዴግ ዘረኛ ስርአት ነው። የሱን የዘረኝነት አባዜ የማይቀበሉትን ሁሉ ማስወገድ እምነቱ ነው። ይህ ደግሞ በውጭ በሚኖረው ዜጋ ሊሞከር የማይችል አጉል ቅዠት ይመስለናል። በዚያ ምትክ አፈላልጎ ያገኘው አዲስ ባይሆንም ተወልዶ ጥርስ የነቀለበትን የዘረኝነትና ጎጠኝነት አስተሳሰብን በቻለው ሁሉ ማዳረስ በመሆኑ። በዚህ እርዮት ለሀያ አመታት ተምረውና ተፈትነው የተዋጣላችው የሚባሉትን በሹመት ሳቢያ ወደውጩ አለም መላክ ነው። የውጭ ጉዳዩን ስዩም መስፍን ወደ ቻይና ሲልክ ግርማ ብሩን ወደዋሽንግተን ካሱ ኢላላን ወደ ኒውዮርክ ሸኝቷል። ይስራ አይስራም የወያኔውን አዲስ የውጊያ ስልት ግን ለማወቅ ብዙ ከባድ አይደለምና፤ ከነዚህ ሹመኞች ጋር ተያይዞ በሙከራ ላይ ያለው በ.አ.ዴ.ን (ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በሚል መሪወቹ ኤርትራዊው በረከት ስመኦን፣ የደቡቡ ተፈራ ዋለዋ፤ ኦሮሞኛ ተናጋሪው አዲሱ ለገሰ፣ በትግራይ ሰውነት የሚታወቁት ታደሰ ጥንቅሹ፣ እንወይ ገ/መድሕን፣ ሕላዊ ዮሴፍ እና መሰል ዘረኞች ሲሆኑ በዚህ ድርጅት ስር በውጭ መደራጀት ላይ ያለው አ.ል.ማ ከምንግዜውም በላይ እንቅስቃሴ ላይ ተሰማርቷል። እንግዲህ ይህ ድርጅት ነው አቶ ታየን (አዲስ ለአምባሳደርነት የተሾመ) ጠርቶ በከተማችን ተሞክሮ የነበረውን ስብሰባ የጠራው።
በአስገራሚ ገጽታው በዚህ ስብሰባ የታዘብነው ቤተክርስቲያን ከሰው በግድ ከምእመን ለመንጠቅ እየሞከሩ ያሎት ግለሰቦች አስተናጋጅና ጋባዥ ሆነው ስናይ አዝነናል። ሌሎችን ፖለቲካ ሰሩ እያሉ እነሱ ከፖለቲካም አልፎ የከፋ የዘር ፖለቲካ ሲሰሩ ስናይ ምን ለማለት እንደፈለጉ ተረድቶናል። ይህን የጠነባ የዘረኛ ስርአት የማይቀበልን መስደብ ማዋረድ ይሁነኝ ብለው የያዙት ስራ ሲሆን። በሰላም ወሎ በሰላም ጸልዮ የሚገባውን ሁሉ ይህን መንግስት ያልተቀበለ አይኑ ላፈር ሲሉን እያየን ነው።
ከዚህ በታች የተጻፈው ስንኝ የተወሰደው ከቤተክርስቲያን ከሳሽ አንዱ ከሆኑት ብሎግ ሲሆን። እንዲህ ይነበባል።
"ቤተክርስቲያን እናት ነችና እናት እንዴት ትከሰሳለች?" እያሉ ለሚጠይቁ ግን ያገሩን ሕግ ካለማወቅ የመጣ ጥያቄ በመሆኑ እናት መከሰስ አይደለም የእናትነት ግዳጇን ካልተወጣች የእናትነት መብቷ ተገፎ ልጆቿን እንደምትነጠቅ መጠቆም እንወዳለን።ቤተክርስቲያንን እናስተዳድራለን ብለው በደል የሚፈጽሙትን ደግሞ ከመክሰስ ሌላ አማራጭ አይኖርም። አማራጭ ቢኖር በጉልበት መፋለም ይሆናል። ያንን ደግሞ እኛ አጥብቀን እንቃወማለን
በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል የተጀመረው ወጣት ተረካቢ ትውልድ ለማውጣት እየተካሄደ ያለው እርብርቦሽ ገሐድ ሆኖ እያለ፤ ካፈርሁ አይመልሰኝ በሚያሰኝ አስገማች መጣጥፋቸው ከዚህ በታች ያለውን አስቀምጠዋል። ይህ ሕጻናትን ለማስተማርም ሆነ ያደጉ ወጣት ልጆቻችንን በግብረገብነት ለማውጣት የተጀመረው ልፋት ለኒህ ጸሐፊ እሳቸውና መሰሎቻቸው እስካልመረቁት ድረስ ዋጋ እንደሌለው በቀላል አማርኛ ይጠቅሳሉ።፡ወገን እንዲመለከተው የምንፈልገው፤ ልጆቻችንን ለማስተማርና ለአስተማሪነትም ብቁ የሆነ ምምሁር ለማፈላለግ የወሰደውን ጊዜ፣ ለዚህ የተባረከ አላማ አስፈጻሚ ሆነው የተመደቡ ሰወች፣ ያጠፉትን ጊዜ ሁሉ ከውሃ ጨምረው ከዚህ በታች ያለውን ሲያስነብቡን የግለሰቡ ፍላጎትና አላማ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ከባድ አልሆነልንም። ለዚህ ግልጽ የሆነ ጽሁፋቸው ሳናመሰግን አናልፍም።
አባትና እናት እየበተኑ፡፡ ወላጆችን ከቤተክርስቲያን እያባረሩ። ልጆቹን እያስተማርን ነው ብለው ሲናገሩ አይቀፋቸውምን?የልጆች ነገር አይሆንልኝም የሚሉት አዛውንትስ የወላጆችን መበተን በጸጋ መቀበላቸው ለምን ይሆን? የሚፈሩት ነገርስ ምንድነው? ይህ ባደባባይ የሚነገር ጥያቄ ሆኖ እየሰማነው ነው።
ማንም የኦርቶዶክስ አማኝ የሆነና በመቅደስ ፊት የቤተክርስቲያኗን እምነትና አምልኮት ለማስተማር በተነሳ አባት ላይ ይህን አይነት ከመስመር የወጣ ትችት ሲመለከት ምን ሊያስብ እንደሚችል መገመት እኒህ ጸሐፊ ምን ያህል ቢሳናቸው ነው ይህን ሊያስነብቡን የደፈሩ?
ባለፈው ሳምንት ካህኑ "ልጆቼንና ባለቤቴን ሸጠህ ትምህርት ቤት አሰራ" ብለውኛል ተብሎ ከመቅደስ ሲነገር ተገርመን ነበር። ቤተክርስቲያናችን የሰውን ልጅ መሸጥና መለወጥ የማትደግፍ መሆኗን አለማወቅም አስመስሏል።ነገሩ ለአባባል ተብሏል ሊባል ይችል ይሆናል። ነገር ግን የሚነገሩ ቀልዶች የሚያመጡት መዘዝ እንዳላቸው ማሳሰብ ፈልገን ነው። ያንን ማየት መረዳት ደግሞ የማመዛዘን እውቀትን ይጠይቃል።
ይህንንም ወደፍርድ ቤት ለመውሰድ ታስቦ ነው ወይስ ለፌዝ? ለምን ጸሐፊው ሙሉ ቃሉን አልጻፉም? አንድ ሙሉ አረፍተነገር ከእናት ሐሳቡ ተቆርጦና ተነጥቆ ሲቀርብ ልዩ ትርጉም ለመስራት እንደሚችል ፊደል የቆጠረ ሁሉ የሚስተው አይደለም። የዚህን ጽሁፍ አቅራቢም ሆነ “የሰላም አፈላላጊ” የተባሉ ተባባሪወቻቸውን እንዲህ አይነት አጉራ ዘለልና ጥራዝ ነጠቅ ለማንም የሚያኮራ ሳይሆን ሁላችንንም የሚያዋርድ አጸጻፍ ባልሞከሩ ምን ያህል ደግ ነበር?
ጸሐፊው ወረድ ብለው በተቆጣና ተራ በሆነ አነጋገር እንዲህ ይላሉ። የተሰዳቢውን ስም የሰረዘው ይህ ጸሐፊ ተራ ዘለፋ እራስን የሚያዋርድ መሆኑን በጥብቅ ስለሚያምን ነው።
ስካር መንፈስ በየመጠጥ ቤቱ እደባደባለሁ እገላለሁ እያሉ የሚጋበዙት የቅንጅቱ አቶ ,,,,,, ዛሬ የትጥቅ ትግል ያሉበትን ያልያዙትን ጠመንጃቸውን ጥለው መስቀል ይዘው ማየታችን ቢገርመንም ይህ ደግሞ ለመልካም ሆኖላቸው ከስካር ቢያድናቸው መልካም በሆነ ነበር። እንደ ቅንጅቱ ማሕተም የቤተክርስቲያኑን ማሕተም ለንግድ ማዋል ይቻላል ብለው በማሰብ ገብተው ከሆነ እንደማይሳካላቸው ካሁኑ ሊነገራቸው ይገባል።ለማንኛውም በዛሬው እለት በመለከት ጦማር ላይ የወጣው የሽማግሌዎችና የአማራጭ አፈላላጊ ኮሚቴ የመጨረሻ ስብሰባ ያረጋገጠልን ነገር ቢኖር ተመራጮቹ ሰላምን እንደማይፈልጉ ቀደም ብለን የተናገርነውን ማረጋገጡ ብቻ ነው። ሽማግሌዎቹ ካሁን በኋላ ያላቸው ምርጫ ቢኖር ብዙሃን ምእመንን ተቀላቅለው በሕግ መፋለሙን መቀጠል ብቻ ይሆናል
ከምር የግል ጥያቄ ነው። በምን የሞራል ሚዛን ነው ለሌሎች መብት ለመከራከር ስል ፍርድ ቤት ሄድሁ ያሉት የዚህ ጸሐፊ የሌላ ግለሰብን መብት ለማዋረድ የተነሳሱት? እንወቃቀስ ከተባለ ከብልግናና አጉራ ዘለል የመንገድ ቋንቋ መውጣት የመጀመሪያ ስራችን በሆነ። ያም ሳይሆን እንዴት የእምነት ቤትን ፍርድ ቤት በዚህ አይነት አነጋገር ለማቆም ተነሳሱ ብለን መጠየቅም መተቸትም እንደአንድ የዚህ ኮሚውኒቲ አባልነታችን ይገባናልና ነው።
No comments:
Post a Comment